የሰላም አመቻች ካውንስሉ ወደ ተግባር እንዲገባ የመንግሥት ሠራተኞች የድርሻቸውን እንዲወጡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን የሰላም ካውንስል ጥሪ አቀረበ፡፡

61

ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የምሥራቅ ጎጃም ዞን የመንግሥት ሠራተኞች ”ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የሰላም ኮንፈረንስ አካሂደዋል።

በአማራ ክልል ላለፉት ጊዜያት አጋጥሞ የቆየውን ግጭት በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት ከክልል ጀምሮ በየደረጃው የሰላም ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ የሰላም ካውንስሉ ክልሉ ያጋጠመውን ችግር በራሱ አቅም እንዲፈታ የተቋቋመ ገለልተኛ የሰላም አመቻች መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የሰላም ካውንስሉ በዞኑ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ ድልድይ በመኾን እያገለገለ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ በመኾኑም የመንግሥት ሠራተኛው ሰላምን ለማምጣት በተዘረጉ አሠራሮች ገንቢ ሃሳቦችን በመስጠት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን የሰላም ካውንስል ሠብሣቢ በቀለ መንግሥት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወንድሞች መንግሥት ያደረገውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይዎት እንዲመለሱ ለማድረግ ካውንስሉ የተጣለበትን አደራ በአግባቡ ለመወጣት ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።

ግጭት ቆሞ ሰላም እንዲሰፍን ማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎችም በዞኑ ባለፉት ጊዜያት አጋጥሞ የቆየው የሰላም እጦት መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የተመሠረተው የሰላም አመቻች ካውንስል ጥረት ዳር እንዲደርስ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋየ በላይ ሰላም በጋራ የሚረጋገጥ የጋራ ሃብታችን ነው ብለዋል፡፡

ያለፈው ግጭት ካደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ትምህርት በመውሰድ ሁሉም ወገን አሸናፊ እንዲኾን ጠንካራ ትብብር ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበ102 ሐሰተኛ የመንጃ ፈቃድ ተጠቃሚዎች ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዷል፡፡
Next article“ጠንካራ ዲሞክራሲ መሠረት ላይ የቆመ ሀገር እንዲኖር እና በእኩልነት ለመዳኘት ጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል” ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)