
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ በተገኙባቸው 102 አሽከርካሪዎች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትራንስፖርት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ለመከላከል ባደረገው ማጣራት ከ243 መንጃ ፈቃዶች ውስጥ 102 የሚኾኑት ሐሰተኛ መኾናቸውን በማረጋገጥ የገንዘብ ቅጣት እና የእግድ እርምጃ መውሰዱን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትራንስፖርት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ሕጋዊ ኾኖ መሥራት ከሐሰተኝነት መጽዳት ነው ያለው የባጃጅ አሽከርካሪው መኮንን ዓለሙ አሽከርካሪነት ጥንቃቄ እና ኀላፊነትን ጭምር የሚጠይቅ ሙያ መኾኑን በመረዳት ከሕገ ወጥ መንገድ መውጣት አለብን ብሏል።
”ባልሰለጠኑበት ሙያ እና ሥራ መሠማራት ከኪሳራው ባሻገር ሙያውንም እንደመናቅ ይቆጠራል“ ያለው አሽከርካሪ ደግሞ ይመር ወንድሙ ነው። ሹፍርና በድፍረት የሚሠራ ሳይኾን ሕጋዊነትን እና ሙያዊ ክህሎትን የሚጠይቅ ሥራ መኾኑንም አክሏል።
ከወረዳዎች ጋር ተቀናጅተው በሠሩት የተጠናከረ ሥራ ከ243 መንጃ ፈቃዶች ውስጥ 102 የሚኾኑት ሐሰተኛ መኾናቸውን በማረጋገጥ የእርምት እርምጃ መውሰድ መቻላቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትራንስፖርት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘውዱ የኋላው ተናግረዋል።
በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክሩ የነበሩ አካላትን ይማሩበታል፤ ሌላንም ያስተምራል፤ በማለት በመመሪያው መሠረት እያንዳንዱን አጥፊ 5 ሺህ ብር በመቅጣት 510 ሺህ ብር ለልማት እንዲውል መደረጉንም ገልጸዋል።
ኀላፊው በዚህ ዓመት ብቻ 44 የትራፊክ አደጋ ተከስቶ የ26 ሰዎች ሕይዎት ማለፉን ገልጸው የትራፊክ አደጋ የብዙዎችን ሕይዎት የሚያሳጣ በመኾኑ ራሳችንን ከአደጋው ልንጠብቅ ይገባል ብለዋል።
ወላጆች ልጆቻቸውን ሕጋዊ መንጃ ፈቃድ ይዘው እንዲያሽከረክሩ እና መላው ሕዝባችን እንዲሁም መንግሥታዊ እና ግብረ ሰናይ ተቋማት በትራፊክ አደጋ የሚከሰተውን ሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት በመከላከል በኩል የድርሻቸውን እንዲወጡ ኀላፊው መልዕክት ማስተላለፋቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ኮሚዩኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!