“በበጀት ዓመቱ ከ4 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል” የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ

38

ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፍትሕ ሥርዓቱን ፈጣን እና ቀልጣፋ ለማድረግ ዘመናዊ አሠራሮችን እየተገበረ መኾኑን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታውቋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ ፍትሕና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን የአሥፈጻሚ አካላትን የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

የፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም የተቋማቸውን የሥራ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።

ኀላፊው በሪፖርታቸውም የአቅም ግንባታ ሥራ ቁልፍ ተግባር አድርገው መሥራታቸውን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመኾን እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ከጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፖሊስ ኮሚሽን እና ከማረሚያ ቤቶች ጋር በመኾን የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ቅንጅታዊ ሥራዎችን በተመለከተ ጥናት መደረጉን እና በጥናቱ መሠረት ወደ ሥራ ለመግባት እየሠሩ መኮናቸውን ነው የተናገሩት። የንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር መሥራታቸውንም ገልጸዋል።

የፍትሕ ሪፎርም ላይ በትኩረት መሠራቱን ነው የገለጹት። ከፍትሕ ሪፎርም አንጻር ነባር እና ደካማ አሠራሮችን ማስተካከል እና በአዲስ አሠራር መቀየር፣ እስካሁን የሌሉ አዳዲስ አሠራሮችን መጨመር፣ ኋላቀር አሠራሮችን ማዘመን እና የሰው ኀይሉን ማብቃት እና ማጥራት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የማኅበራዊ ፍርድ ቤት ኀላፊነትን የመፈተሽ ሥራ እና የማኅበራዊ ፍርድ ቤት አቅምን ለማጎልበት መሠራቱንም ተናግረዋል። የአቅም ማነስ፣ የፍላጎት ማነስ እና በሥነ ምግባር ችግር የተገኘባቸው አካላትን ከኀላፊነት የማንሳት እና ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው የተባለው።

የፍትሕ ሥርዓቱን ፈጣን እና ቀልጣፋ ለማድረግ ዘመናዊ አሠራሮችን መተግበር መጀመሩንም ተናግረዋል። ኋላቀር አሠራርን መቀየር አንደኛው የለውጡ አካል ነው ያሉት ኀላፊው የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እያሳደጉ እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት።

አሠራሩን ማዘመን፣ የውሸት ሪፖርት እንዳይቀርብ እና ሌሎች ኋላ ቀር አሠራሮች እንዲቀሩ ያደርጋል ነው ያሉት። አዲስ የጣቢያ እና የማረሚያ ቤቶች ጉብኝት ማድረጊያ ማንዋል እየተዘጋጀ መኾኑንም ተናግረዋል። የማረሚያ ቤት ታራሚዎች የንቃተ ሕግ ትምህርት መስጫ ማንዋል አዘጋጅተው ወደ ሥራ እየገቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

በይቅርታ አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ ሃሳብ ያለው አሠራር ማዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።

ያልተሻሻለውን የፍትሐ ብሔር አሠራር ማንዋልን የማሻሻል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የድርድር ደንብ በማውጣት የመንግሥት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ድርድር ለመጨረስ የሚያስችል አሠራር ደንብ እየተዘጋጀ ነው ተብሏል።

የነጻ ሕግ አገልግሎት አሰጣጥ ማንዋልም እየተዘጋጀ መኾኑን ነው ኀላፊው የተናገሩት። በበጀት ዓመቱ ለ502 ነጻ የሕግ አገልግሎት እና ለ14 ተቋማት የሕግ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን የወንጀል መዛግብት መከታተል እና መሥራት የሚያስችል አሠራር ማስቀመጣቸውንም ገልጸዋል። የፍትሕ ተቋማትን ተደራሽነት ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያሉት ኀላፊው ኅብረተሰቡን በንቃተ ሕግ ትምህርት ላይ እንዲሳተፍ ለማድረግ አሠራር መለየቱን ነው ያነሱት። የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ የምስክሮችን ደኅንነት መጠበቅ አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ 13 ሺህ 772 መዝገቦች መቅረባቸውን ያነሱት ኀላፊው 13 ሺህ 397 መዝገቦች ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል ነው የተባለው። 15 ሺህ 671 መዛግብትን ለፍርድ ቤት አቅርበው 6 ሺህ 863 መዝገቦች ውሳኔ አግኝተዋል ነው ያሉት። የፍትሕ ቢሮ የማሸነፍ አቅሙ ከፍ እያለ መምጣቱንም ተናግረዋል።

አቤቱታ የማዳመጥ እና መልስ የመስጠት ችግሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ያለ አግባብ የሚታሠሩ ሰዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው ይሄን አካሄድ ማስተካከል ይገባልም ብለዋል።

ፍትሕ ቢሮ ወንጀለኞችን ማስቀጣት ብቻ ሳይኾን ሃብት የማሠባሠብ ሥራም ይሠራል ነው ያሉት። በርካታ የመንግሥትን የገንዘብ ምዝበራ ማስቀረታቸውንም አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱ በሁለት ዙር ለ4 ሺህ 201 ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል። የፍትሕ ሥርዓቱን ቀልጣፋ ለማድረግ እና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች በቀጣይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ችግኝ መትከላችን አፈርን በማቀብ መሬትን ለትውልድ እንድናሻግር ያስችለናል” የሰሜን ወሎ አርሶ አደሮች
Next articleየወልድያ ከተማ አሥተዳደር የ2016 የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላን አስጀመረ።