
ወልድያ: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በሰሜን ወሎ ዞን በሁሉም ቀበሌዎች፣ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ተጀምሯል።
“የሚተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ የ2016 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ይገኛል።
የሰሜን ወሎ ዞንም በሀብሩ ወረዳ አብዮት ፍሬ ቀበሌ መርሐ ግብሩን በይፋ ጀምሯል።
በዚህ ዓመት ከ150 ሚሊዮን በላይ የደን እና ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ተገኘ አባተ ገልፀዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ በሪሁን የተተከሉ ችግኞችን ማኅበረሰቡ ይንከባከብ ዘንድ አሳስበዋል።
በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በሰሜን ምሥራቅ እዝ የ802ኛ ኮር አዛዥ ኮሎኔል ቢራራ ሙንዬ መጥፎ አስተሳሰብን በሰናይ ምግባር መሻርን ዓላማ ያደረገ የችግኝ ተከላ ሠራዊታችን በማከናወኑ ደስተኞች ነን ብለዋል።
በመኾኑም ከደጉ ሕዝባችን ጋር ኾነን ጥላቻን ነቅለን ፍቅርን ተክለናል ብለዋል።
በችግኝ ተከላው ያገኘናቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው “ችግኝ መትከል አፈርን በማቀብ መሬታቸውን ለትውልድ ማሻገር እንደሚያስችላቸው ” ገልጸዋል።
አርሶ አደሮቹ የአየር ንብረት ሚዛን በመጠበቅ ሚናው ጉልህ ነው፤ ፍራፍሬም ብንተክል ቀጥታ ተጠቀሚ ያደርገናልና ችግኝ በመትከላችን ደስተኞች ነን ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!