የሰላም ካውንስል ኮንፈረንስ በጎንደር ከተማ ተካሄደ።

24

ጎንደር: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሰላም ካውንስል ኮንፈረንስ አካሂደዋል፡፡

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች፣ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከሚገኙ ቀበሌዎች እና ክፍለ ከተማዎች የተውጣጡ ናቸው፡፡

ተሳታፊዎቹ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን ለመወጣት እና የሰላም ካውንስሉ ያስቀመጠውን የሰላም ጥሪ ውጤታማ እንዲኾን እንደሚጥሩም ገልጸዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የጎንደር ከተማ ሰላም ካውንስል ዋና ሠብሣቢ ቆሞስ አባ ዮሴፍ ደስታ ባደረጉት ንግግር በክልል የተመሠረተው የሰላም ካውንስል ግቡን እንዲመታ በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ የማቋቋምን ተገቢነት አብራርተዋል።

ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የሠላም ካውንስል አባላት ሠላም ያመጣሉ ተብለው በሕዝቡ የተመረጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

ከታች አርማጭሆ ወረዳ ከመጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ የኾኑት አቶ ታመነ ተሻገር “የሀገር ሽማግሌዎች ሰላም እንዲመጣ ሚናችንን ልንወጣ ይገባናል” ሲሉ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

ከጎንደር ከተማ የተወከሉት አቶ ማማሩ ዘላለም በበኩላቸው ድርድሩ መዘግየቱን ገልጸው የሰላምን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ በማስረጽ ሕዝቡ ለሰላም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ የተቻላቸውን ሁሉ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ተስፋየ አይጠገብ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዞኑ ችግኝ መትከል ከጊዜ ወደ ጊዜ ባሕል እየኾነ መጥቷል” የሰሜን ጎንደር ግብርና መምሪያ
Next articleየወባ በሽታን ለመከላከል