“በዞኑ ችግኝ መትከል ከጊዜ ወደ ጊዜ ባሕል እየኾነ መጥቷል” የሰሜን ጎንደር ግብርና መምሪያ

35

ደባርቅ: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዘንድሮው የአረጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 42 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ እየተተከለ ነው፡፡

የሰሜን ጎንደር ግብርና መምሪያ እንዳስታወቀው የ2016 ዓ.ም የአረጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

የመምሪያው ኀላፊ ጌታቸው አዳነ ችግኝ የማፍላት፣ የመትከያ ቦታ የመለየት እና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።

በዚህም ከ 42 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ምጣኔ ሃብታዊ እና ሥነ ምህዳራዊ ፋይዳ ያላቸው የተለያዩ ችግኞች መዘጋጀታቸውን እና 6 ነጥብ 5 ሄክታር የመትከያ ቦታ መለየቱን ገልጸዋል።

ኀላፊው በዞኑ ችግኝ መትከል ከጊዜ ወደ ጊዜ ባሕል እየኾነ መምጣቱን ገልጸው በዚህ ዓመት ለተከላ የተዘጋጀውን 42 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ለመትከል ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።

ከዚህ ውስጥም በአንድ ቀን ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱንም አንስተዋል፡፡

እስካሁን በተከናወነ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 57 ሺህ 400 በላይ ችግኞች መተከላቸውንም ጠቁመው ተከላው እስከ ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

እንደ ዞን የተተከለውን በመንከባከብ፣ ከንክኪ ነጻ በማድረግ እና በማጽደቅ ረገድ ውስንነት መኖሩን የጠቆሙት ኀላፊው የተስተዋለውን ችግር በመቅረፍ በቀጣይ የሚተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን ለመጨመር ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን ብለዋል።

በተከላ መርሐ ግብሩ የተሳተፉ አርሶ አደሮች በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች ለአርሶ አደሩ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል። አፈሩን ደግፈው በመያዝ ከመሸርሸር የሚከላከሉ፣ ሲያድጉ ቅጠላቸው ለእንሰሳት መኖነት፣ ፍሬያቸው ለምግብነት የሚውሉ በመኾናቸው ችግኝ መትከል ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

ከመንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው አስፈላጊውን ጠቀሜታ እንዲሰጡ የመንከባከብ እና ከንክኪ ነጻ የማድረግ ሥራ እንሠራለንም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ11 ሺህ በላይ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ማኅበረሰቡን መቀላቀላቸውን የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
Next articleየሰላም ካውንስል ኮንፈረንስ በጎንደር ከተማ ተካሄደ።