
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን የአሥፈጻሚ አካላትን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸማቸውን እየገመገመ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው የቢሯቸውን እና የተጠሪ ተቋማትን የሥራ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም በዓመቱ የታቀደውን ዕቅድ ከመፈጸም ይልቅ በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማርገብ ሢሠሩ መክረማቸውን ተናግረዋል። የጸጥታ ችግሩ መደበኛ ዕቅዶችን ለመፈጸም እንቅፋት ኾኖባቸው መቆየቱን ነው የተናገሩት።
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ክልሉን ዘርፈ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለው ተናግረዋል። ክልሉ በውጫዊ እና በውስጣዊ ፈተናዎች መፈተኑን ገልጸዋል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በአንድ ጊዜ የተነሳ ሳይኾን በብዙ ውጫዊ እና ውስጣዊ ግፊቶች የተነሳ እንደኾነም ተናግረዋል።
በክልሉ ከቆየው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ባለፈ በሱዳን የተፈጠረው ጦርነት በርካታ ስደተኞች ወደ ክልሉ እንዲገቡ ማድረጉን እና ጫና እንዲፈጠር ምክንያት መኾኑን ተናግረዋል። በማይካድራ ንጹሐንን ገድሎ ወደ ሱዳን የሄደው የሳምሪ ቡድን ክልሉ ሰላም እንዳይኾን እንቅስቃሴ ማድረጉንም ገልጸዋል።
በአጎራባች ክልሎች የአብሮነት እና የወንድማማችነት አቅም እንዲዳብር ዕቅድ ይዘው ወደ ሥራ መግባታቸውንም አስታውሰዋል። በሱዳን እና በአጎራባች ክልሎች የሚፈጠሩ ጫናዎች በክልሉ ለተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተጫማሪ ተግዳሮት መኾናቸውን ነው ያነሱት።
የአማራ ክልል ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በጸጥታ ችግር ውስጥ እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊው በውጭ እና በውስጥ ኀይሎች ግፊት በሕዝብ የተመረጠ መንግሥትን ለማፈረስ ጥቃት መድረሱን ነው የተናገሩት።
የክልሉን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የጸጥታ መዋቅርን ማጠናከር፣ የጸጥታ ኀይሉን ማሠልጠን እና መልምሎ እንዲደራጅ መደረጉንም ገልጸዋል። የጸጥታ መዋቅሩ የመልካም አሥተዳደር ችግርን እንዲፈታ መሠራቱንም ተናግረዋል።
ለፖለቲካ መሪዎች ሥልጠና እና መልሶ ማደራጀት መሠራቱንም አስታውቀዋል። ነገር ግን የነበረው የተዛነፈ አመለካከት የክልሉን የጸጥታ ችግር ውስብስብ አድርጎት መቆየቱን ነው የገለጹት።
የጸጥታ መዋቅር ለሕዝብ ሰላም መስዋዕትነት መክፈሉን እና እየከፈለ መኾኑንም ተናግረዋል። ሕይዎቱን፣ ቤተሰቡን እና ሃብቱን እያስያዘ የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት የሰጠውን ኀላፊነት ለመወጣት መዋደቁንም አስታውቀዋል። የተለየ ድጋፍ ሳይደረግላቸው በዓላማ ጽናት እና በቃል ኪዳን የጸኑ ጀግኖች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
የክልሉ የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሉን የተናገሩት ኀላፊው አሁንም የክልሉን ሰላም የሚያውክ ግጭት መኖሩን ነው የገለጹት። የመንገድ መዘጋት፣ የንጹሐን መታገት፣ መገደል፣ የግብዓት አቅርቦት እንዳይኖር የማድረግ ችግር መኖሩን ነው የተናገሩት። የጸጥታ ኀይሉ በሠራው የተቀናጀ ሥራ የግብዓት አቅርቦት እንዲሠራጭ መደረጉንም ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቶች ላይ፣ በገበያ ቦታዎች እና ንጹሐን በሚሠባሠቡባቸው ሥፍራዎች ቦንብ የማፈንዳት የሽብር እንቅስቃሴ እንደነበር ነው ያስታወሱት። ባለሃብቶች ላይ እየተፈጸመ ባለው እገታ በርካታ ባለሃብቶች ክልሉን ለቀው እንዲሰደዱ መገደዳቸውንም ገልጸዋል።
የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት እንዲነሳ በስፋት የሚሠሩ ኀይሎች እንደነበሩም ተናግረዋል። የክልሉ ሕዝብ መጀመሪያ ከነበረበት መደናገር በመውጣት ለሰላም አበክሮ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲቀጥል፣ ማድረጉን ተናግረዋል። የጸጥታ ኀይሉን መልሶ ከማደራጀት ባለፈ የሕግ ማስከበር ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።
ከ11 ሺህ በላይ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው መግባታቸውንም ተናግረዋል። በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ ወገኖች የተሃድሶ ሥልጠና እየተሰጣቸው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውንም አስታውቀዋል።
የሰላም እሴት ግንባታ እና ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የታቀደው ዕቅድ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሚፈለገው ልክ አለመሠራቱንም ገልጸዋል።
የጸጥታ ተቋሙ በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በማርገብ፣ አካባቢውን በማረጋጋት እና የክልሉ መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲመጣ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረውም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!