
አዲስ አበባ: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በሀረር ከተማ ተገኝተው ለክልሉ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚውል የ20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።
ሚኒስትሯ ከተሞች የመልማት አቅማቸውን ከተጠቀሙ ለሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ከ 50 በመቶ በላይ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ሁሉም በተፈጠረላቸው አቅም እኩል ማደግ እንደሚችሉም አሁን ላይ በከተሞች እያየነው ያለው ለውጥ ምስክር ነው ያሉት ሚኒስትሯ ለዚህም መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በሀረር ከተማም ያለው መነቃቃት ከተማዋን ውብና ፅዱ የማድረግ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎች ለሌሎች ክልሎች ምሳሌ የሚኾን ነው ብለዋል ሚኒስትሯ። ከተሞች የሚለሙት ለነዋሪዎች በመኾኑ ነዋሪዎች ለልማቱ ተሳታፊና ደጋፊ መኾን እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
የሀረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ የሀረርን እድሜ በሚመጥን መልኩ ለነዋሪዎችና ለጎብኝዎች ምቹ ለማድረግ የተለያዩ ሰው ተኮር የኾኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እንደ ኮሪደር ልማት፣ የከተማ ጽዳትና ውበት፣ የአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል።
በዚህ ሂደትም ማኅበረሰቡ ደስተኛ በመኾኑ ለልማቱ አጋዥ ነው። አበረታች ግብረ መልስም እያገኘን ነው ብለዋል።
በክልሉ የተጀመረውን የሰው ተኮር ተግባር ለማስቀጠልም የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ድጋፍ አስተዋፅኦው ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ በሀረር ቆይታቸው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርና የአቅመ ደካሞች ቤትን የማደስ ሥራ አስጀምረዋል::
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወደ 500 ለሚጠጉ ተማሪዎችም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል። በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች የተሠሩ የልማት ሥራዎችንም ተዟዙረው ተመልክተዋል።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!