ከቴክኖሎጂ ማስፋፋት ባለፈ በአረንጓዴ አሻራ ሥራ ለ4 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወደ ሥራ መግባቱን ኢትዮ ቴሌኮም ገለጸ፡፡

28

ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም በዘንድሮው ዓመት ለስድስተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ግማሽ ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል።

ከሀምሌ 11/2016 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ቀናት የችግኝ ተከላ ሥራ እንደሚከናወን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ ተናግረዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኝ በመላው ሀገሪቱ በተቋሙ እና በአጋር ድርጅቶች መትከላቸውን የተናገሩት ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ ለ20ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም አንስተዋል። ለዚህም 124 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ሀገሪቱን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እንሠራለን ያሉት ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ ዛሬ በተጀመረው የአረንጓዴ ኢትዮጵያ አሻራ ግማሽ ሚሊዮን ችግኝ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 698 የችግኝ መትከያ ቦታዎች ዝግጁ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ዘንድሮ ለሚተከሉት ችግኞች ማስፈጸሚያ 50 ሚሊዮን ብር መመደቡን እና ለ4 ሺህ ዜጎችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወደ ሥራ መገባቱንም አስረድተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን የተተከሉትን ችግኞች በመንከባከብ የጽድቀት መጠኑን 85 ለማድረስ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክረምት ወራት የኮሌራ በሽታ እንዳይከሰት በንቅናቄ እየሠራ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ ጤና መምሪያ አስታወቀ።
Next articleከባሕር ዳር ኮምቦልቻ እና ከኮምቦልቻ ባሕር ዳር በረራ ሊጀመር ነው።