“ችግኞችን ከመትከል ባሻገር ብሔራዊ ፓርኮችን እና ጥብቅ ደኖችን መጠበቅ ይገባል” የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ

40

ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በየዓመቱ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ምህዳራዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞችን ከመትከል ባሻገር በዞኑ የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮችን እና ጥብቅ ደኖችን መጠበቅ ይገባል ሲል የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አሳስቧል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የ2016 በጀት ዓመት የአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብርን በገንዳ ውኃ ከተማ አስጀምሯል።

ምዕራብ ጎንደር ዞን ከ624 ሺህ በላይ የሚኾነው መሬት በደን የተሸፈነ ሲኾን አረንጓዴ መቀነት እየተባሉ የሚጠሩት የአልጣሽ እና የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም የማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም ጥብቅ ደን ሰፊውን ቦታ እንደሚይዙ የዞኑ አሥተዳዳሪ ቢክስ ወርቄ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ በየዓመቱ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ምህዳራዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞችን ከመትከል ባሻገር እነዚህን ነባር ደኖች ከሰው ሠራሽ አደጋዎች መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባውም ተናግረዋል።

መምሪያው ሥነ ሕይዎታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ለጥምር ግብርና ጠቀሜታ ያላቸው ሀገር በቀል ችግኞችን በየዓመቱ በማፍላት እየተከለ መኾኑን የመምሪያ ኀላፊው አንዳርጌ ጌጡ ገልጸዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብር ከ572 ሺህ በላይ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

ለተዘጋጁት ችግኞችም ከ500 ሄክታር በላይ መሬት ተዘጋጅቷልም ነው ያሉት፡፡

የዞኑ የደን ሽፋን 36 ከመቶ መኾኑን ጠቅሰው ሽፋኑን በ0 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አቶ አንዳርጌ ጠቁመዋል።

እንደ መምሪያ ኀላፊው ገለጻ የሚተከሉት ችግኞች የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ከማስጠበቅ፣ ምርት እና ምርታማነትን ከመጨመር ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው። ከነዚህ ውስጥም እንደ አካሻ ሴኔጋል፣ ዋሊያ መቀር (የእጣን ዛፍ)፣ ሽመል፣ ማንጎ፣ ሞሪንጋ (ሽፈራው) እና ሚም ዛፍ ተጠቃሾች ናቸው።

የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ጥበቃ እየተደረገላቸው መኾኑንም ተናግረዋል።

በየዓመቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ሕይዎታዊ እና ሥነ ምህዳራዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞችን ከመትከል ባሻገር በዞኑ የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮችን እና ጥብቅ ደኖችን መጠበቅ እንደሚገባ ነው መምሪያ ኀላፊው ያሳሰቡት።

የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው በዛሬው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ገልጸው ችግኞቹ በዘላቂነት ጸድቀው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የበኩላቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡ ነው የተናገሩት።

በአካባቢያቸው የሚገኙ ጥብቅ ደኖች አደጋ እንዳይደርስባቸውም ክትትል እና ቁጥጥር እያደረጉ መኾኑን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።

በ2015 ዓ.ም ከተተከሉት ችግኞች 75 በመቶ የጽድቀት ምጣኔ መኖሩን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ2 ቢሊዮን 334 ሚሊዮን በላይ የውስጥ ኦዲት ግኝት ውዝፍ ውስጥ 77 በመቶውን ማስመለስ መቻሉን ገንዘብ ቢሮ አስታወቀ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአየርላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ።