ከ2 ቢሊዮን 334 ሚሊዮን በላይ የውስጥ ኦዲት ግኝት ውዝፍ ውስጥ 77 በመቶውን ማስመለስ መቻሉን ገንዘብ ቢሮ አስታወቀ።

24

ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ፕላን እና ልማት ቢሮ፣ ገንዘብ ቢሮ፣ ገቢዎች ቢሮ፣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አሥተዳደር የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

ተቋማቱ በ2016 በጀት ዓመት ያከናወኗቸውን ተግባራት እና ያጋጠሙ ችግሮችን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል። አፈጻጸማቸውን ካቀረቡ ተቋማት መካከል የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ አንዱ ነው።

ቢሮው የቁጥጥር ሥራን በማጠናከር የተጠያቂነት አሠራርን በማጎልበት የመንግሥት ሃብት እና ንብረት አጠቃቀምን ውጤታማ ማድረግ ዓላማ አድርጎ ሢሠራ ቆይቷል ብለዋል የቢሮው ኀላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር)።

ቢሮው በ2016 በጀት ዓመት 2 ቢሊዮን 334 ሚሊዮን 119 ሺህ 862 የውስጥ ኦዲት ግኝት ውዝፍ ውስጥ 77 በመቶውን ማስመለስ መቻሉን አቅርበዋል። ከዘመኑ የውስጥ ኦዲት ግኝት 58 ሚሊዮን 202 ሺህ 601 ብር ውስጥ ደግሞ 58 በመቶ ማስመለስ ተችሏል ብለዋል፡፡

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የፕሮጀክት ሥራዎች በተቀመጠው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ክትትል እና ግምገማ ማድረግ አለመቻል እና የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በከተሞች የግዥ እና ንብረት አሥተዳደር ኦዲት ማድረግ አለመቻሉ ችግሮች እንደነበሩ ተነስቷል።

17 ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች በጀት አጽድቀው መላክ አለመቻላቸው እና የ2015 በጀት ዓመት በጀትን ሂሳብ ለመዝጋት ረጅም ጊዜ መውሰዱ ሌላኛው ችግር እንደነበር ነው የቀረበው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ እንዲጠናቀቅ የሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
Next article“ችግኞችን ከመትከል ባሻገር ብሔራዊ ፓርኮችን እና ጥብቅ ደኖችን መጠበቅ ይገባል” የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ