
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮን የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።
የቢሮው ኀላፊ እርዚቅ ኢሣ ባቀረቡት ሪፖርት ለወጣቶች የግንዛቤ ፈጠራ እና የማደራጀት ሥራ መሠራቱን፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች ለወጣት መሪዎች ተሳትፎ እና ውክልና እንዲኖራቸው መሠራቱን፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ግንዛቤ እና አደረጃጀት መፈጠሩን፣ የቁጠባ እና ብድር አገልግሎት መሠጠቱን አብራርተዋል።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች የደካሞችን ቤት በመጠገን እና በመሥራት፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ ደን እና ሰብል ልማት መሳተፋቸውንም አቶ እርዚቅ ገልጸዋል።
በስፖርቱ ዘርፍ ስኬት እንደተመዘገበ ያመላከቱት ኀላፊው በተለያዩ ዘርፎች የስፖርት ቡድኖች መቋቋማቸውን እና ድጋፍ መደረጉን፣ ለስፖርት ድጋፍ መሠብሠቡን፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን የማስፋፋት፣ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ጠንካራ ተሳትፎ እና ከክልል እስከ ዓለም አቀፍ ድረስ ውጤት ያስመዘገበ ሥራ፣ ውድድሮችን በውጤታማነት ማካሄድ እና መሳተፍ፣ የባሕል ስፖርት ጠንካራ ተሳትፎ እና ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት እንዲሁም የአሠራር ሕጎች እንዲወጡ የማድረግ ሥራ መከናወኑን ቢሮ ኀላፊው ጠቅሰዋል።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ ጥሩ አፈጻጸም ላይ መኾኑን ጠቅሰው ከሀገር ውጭ ያለው የግዥ ሂደት ውስብስብነት፣ የዶላር ምንዛሪ እጥረት፣ የካሽ ገንዘብ በተፈለገው መንገድ አለመገኘት፣ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት እቃዎችን ለማጓጓዝ አለማስቻሉን እንደ እጥረት ጠቅሰው በመጪው ዓመት ሥራው ይጠናቀቃል ብለዋል።
ሪፖርቱን ያዳመጡት የቋሚ ኮሚቴ አባላትም የተቋም ግንባታ እና በሕግ ማዕቀፍ የማጠናከር ሥራውን እና በስፖርቱ ዘርፍ የተሠራውን ሥራ እንዲሁም ውጤቱን አበረታትተዋል።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ በየዓመቱ በጀት እየተያዘለት ነገር ግን አለመጠናቀቁ አሳሳቢ መኾኑን አስተያየት ሰጪዎች አጽዕኖት ሰጥተውታል። ተጠናቀቀ የሚል ዜና በምንጠብቅበት ጊዜ አሁንም በግንባታ ሂደት ላይ ነው መባሉ ክልሉን ለወጪ ዳርጎታል፤ አሁንም አሳሳቢ ነው ተብሏል።
ግንባታው ትኩረት ተሰጥቶት እንዲጠናቀቅም ነው የተጠየቀው። ለስፖርት ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ልክ ለወጣቱ ዘርፍ አለመሰጠቱ እና የማኅበረሰብ ስፖርት ትኩረት አናሳነት በአስተያየቶቹ ተጠቅሰዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሠብሣቢ እመቤት ከበደ የቋሚ ኮሚቴውን የክትትል ሪፖርት አቅርበዋል። በስፖርቱ ዘርፍ የተደረገው ጥረት፣ የተገኙ ውጤቶች እና ባለሃብቶችን በስፖርት ድጋፍ ማሳተፉ በጥንካሬ ከጠቀሷቸው መካከል ይገኙበታል።
የወጣቶች አደረጃጀትን ሥልጠና የመስጠት ውስንነት፣ የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ አነስተኛነት፣ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ መጓተት ደግሞ በእጥረት ከጠቀሷቸው መካከል ናቸው። በቀጣይ በጀት ዓመትም ቢሮው የበለጠ በጥንካሬ እንዲሠራ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!