
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን በበጀት ዓመቱ ግዥ ከተፈጸመለት ሰዉ ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚኾነዉ ወደ ዞኑ መድረሱን አስታውቋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አበበ መኮነን እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በአዲስ ለማቅረብ ግዥ ከተፈጸመለት 1 ሚሊዮን 544 ሺህ 956 ኩንታል ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ውስጥ 1 ሚሊዮን 159 ሺህ 632 ኩንታል ያህሉ ወደ ዞኑ መግባቱን ተናግረዋል።
እስካሁን ለዞኑ ከቀረበዉ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ውስጥ 1 ሚሊዮን 74 ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጭ መደረጉን አቶ አበበ ገልጸዋል።
በአዲስ ከቀረበው ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ውስጥ 94 በመቶ ያህሉ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱም ተገልጿል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2016/17 የምርት ዘመን ከ612 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል በመሸፈን ከ23 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅዶ እየሠራ መኾኑንም ከክልሉ ኮሙኒዩኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!