“አረንጓዴ አሻራ ለነገው ትውልድ የተስፋ እስትንፋስ ነው” የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ቢክስ ወርቄ

31

ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳር የዘንድሮውን ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በገንዳ ውኃ ከተማ ገስት ሃውስ ጥብቅ ደን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል።

በመርሐ ግብሩ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ፣ በጥቂቱ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የሀገራችን ቀደምት ልምላሜዋ እንዲመለስ ለማድረግ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል ።

አረንጓዴ አሻራ ለነገው ትውልድ የተስፋ እስትንፋስ ነው በማለትም ገልጸዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በሚፈጠር የተፈጥሮ ሀብት መራቆት እና መሠል ችግሮች በሀገራት ላይ የደኅንነት ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል፡፡

አረንጓዴ አሻራ ልማትን ለማፋጠን የአርበኝነት ማሳያ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።

ባለድርሻ አካላቱ በዋናነት መትከል ብቻ ሳይኾን ሰለመፅደቁም ክትትልና እንክብካቤ ላይ ጭምር ማተኮር እንደሚገባ የዞኑ አሥተዳደር አሳስቧል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አንዳርጌ ጌጡ እንደተናገሩት፣ በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ አገልግሎት ከ572 ሺህ በላይ ችግኞችን ተከላ ለማከናወን መታቀዱን አመላክተዋል።

በዞኑ ያሉትን እምቅ የተፈጥሮ የደን ፀጋዎች በዋናነት በመጠበቅ እና በማበልፀግ፣ ለተተከሉትም ክትትልና ድጋፉን መምሪያው አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ኃላፊው የገለጹት።

አቶ አንድርጌ የአኬሻ ሙጫ ዛፍ፣ ግራር ፣ ሚምና ልዩ ልዩ የእጽዋት ዝርያዎችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት የተተከሉ የሙጫ ችግኞች ምርት መስጠት መጀምራቸውን ጠቁመዋል።

የገንዳ ውኃ ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ማንደፍሮ ተፈራ፣ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምክንያት እያጋጠማት ያለውን ሥጋት ለመቅረፍ በአረንጎዴ አሻራ መርሐ ግብር ሀብት መፍጠር ይጠበቅብናል ብለዋል።

የልማት ጉዳይ ከደኅንነት ጉዳይ ተነጥሎ የማይታይ በመኾኑ ለተግባራዊነቱ መትጋት እንደሚገባም ኃላፊው አሳስበዋል።

በተከናወነው የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የዞን፣ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ የአጋር በጎ አድራጎትና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሻራቸውን እያሳረፉ ስለመገኘታቸውም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ለውጥ እያመጣ መኾኑን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡
Next article“በአዲስ ከቀረበው ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ውስጥ 94 በመቶ ያህሉ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል” የምሥራቅ ጎጃም ዞን