
ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና አካባቢ ጥበቃና የውኃ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም እየገመገመ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የግብርና ቢሮውን የሥራ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።
የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ማረጋገጥ፣ ለግብርና ኢንዱስትሪ በቂ አቅርቦት ማቅረብ፣ የውጭ ምንዛሬ አቅምን ማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ መገንባት እና ሌሎች የቢሮው አንኳር ጉዳዮች እንደነበሩ ተናግረዋል።
የአረንጓዴ ልማትን በማሳደግ ዘላቂ የግብርና ልማት ማሳደግ፣ የመስኖ አቅምን ማጎልበት፣ የሜካናይዜሽን አቅምን ማሳደግ፣ የእንስሳት ሀብትን ማሳደግ፣ የባለሀብቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ አካታች የግብርና ልማትና ሌሎችም ግብርና ቢሮው በትኩረት ሲሠራባቸው የነበሩ ጉዳዮች መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ኢኮኖሚ የተመሠረተው በግብርና ነው ያሉት ዶክተር ድረስ ግብርና ችግር በገጠመን ጊዜ የሚታደገን ዘርፍ ነውም ብለዋል። ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት መሥጠት እንደሚገባም አንስተዋል። 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን መሬት በማልማት ምርትን በ16 ነጥብ 4 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱንም አንስተዋል።
ለማረስ ከተያዘው 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚኾነው መታረሱንም አስታውቀዋል። ከዚህ ውስጥም ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላዩ በዘር መሸፈኑን ነው የተናገሩት።
ከ59 ሚሊዮን በላይ ሜትር ኪዩቢክ ኮምፖስት መዘጋጀቱንም ገልጸዋል። የጸጥታ ችግሩ የኮምፖስት ዝግጅት ሥራዎችን መጉዳቱንም አመላክተዋል።
በክልሉ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኝ መልማቱንም ገልጸዋል። በዓመቱ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን የወተት ምርት ማምረታቸውንም ተናግረዋል። በስጋ፣ በእንቁላል፣ በቆዳና ሌጦም ሰፋፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።
8 ሚሊዮን 57 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መገዛቱን የተናገሩት ኀላፊው 7 ነጥብ 3 ሚሊዮኑ ጅቡቲ ወደብ መድረሱን ገልጸዋል። “ከ5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል” ነው ያሉት። የስርጭት መጠኑ በየቀኑ እየጨመረ መጥቷል፤ ዘንድሮ አርሶ አደሮችን በማርካት እየተሠራ ነው ብለዋል ቢሮ ኀላፊው። የአማራ ክልል የዘር ስርጭት ከራሱ አልፎ ለአራት ክልሎች ምርጥ ዘር መስጠቱንም አመላክተዋል።
169 ትራክተሮች እና 13 ኮምባይነሮች ተሠራጭተዋል ነው ያሉት። 5 ሺህ 350 ሞተር ፓምፕ ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱም ተመላክቷል። የከተማ ግብርና ልማትን ስትራቴጂ ጨምሮ በርካታ ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።
የሰብዓዊ ድጋፋን በራስ አቅም ለመሸፈን ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል። በአማራ ክልል ከውጭ ድጋፍ ሳይጠየቅ የሚፈጠረውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችል መሬት ለማልማት አቅድ መያዙንም ገልጸዋል። የጸጥታው ችግር ግን ፈተና እንደኾነባቸው ነው የተናገሩት። በግብርናው ዘርፍ በጸጥታ ችግር ውስጥም ኾኖ ከፍተኛ ሥራ መሥራቱንም ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ የሜካናይዜሽን መስፋፋት፣ የስንዴና የአኩሪ አተር ልማት፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት መሻሻል መታየቱንም ገልጸዋል።
በዓመቱ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር፣ የዋጋ ግሽበት በግብርና ሥራዎች ላይ ጫና መፍጠር፣ የግብርና ተቋማት ይዞታ መነጠቅ፣ የአግሮፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች የኃይል እና የውኃ አቅርቦት ችግሮች አለመፈታት ፈተናዎቻቸው እንደነበሩ ገልጸዋል።
የክረምቱን የሰብል ልማት እቅድ ለማሳካት የተጠናከረ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ፣ አረንጓዴ አሻራ ልማትን ማፋጠን፣ የማዳበሪያ ሥርጭትን በወቅቱ ማድረስ፣ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም መሥራት፣ የተቋም ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረግ እና በሁሉም ደረጃ ተናብቦ መሥራትን ማጠናከር የቀጣይ አቅጣጫዎች መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!