“ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን የማሳደግ ኀላፊነትም አለብን” ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ

26

ሰቆጣ: ሐምሌ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ 04 ቀበሌ ቦውሹ ተፋሰስ የመጀመሪያ ዙር ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በችግኝ ተከላው ላይም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኅላፊዎች፣ የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር መሪዎች እና የ04 ቀበሌ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

ችግኝ ሲተክሉ ያገኘናቸው አቶ ሸጋው አስረሱ የቦውሹ ተፋሰስ የእጽዋት መመናመን አጋጥሞት እንደነበር አስታውሰው ባለፉት ዓመታት በተሠራው የችግኝ ተከላ ወደ ነበረ ማንነቱ እየተመለሰ መኾኑን ገልጸዋል።

ችግኝ ለመትከል ብቻ ሳይኾን ለማሳደግም ቆርጠን ተነስተናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ባዩሽ ማሞ ናቸው። “በየዓመቱ የተከልነው ችግኝ ጸድቆ በማየታችን ደስተኞች ነን” ያሉት ወይዘሮ ባዩሽ ተፋሰሱን በጥበቃ በማስጠበቅ እና ከእንሰሳት ንክኪ በማጽዳት ችግኞቹን የመንከባከብ ልምድ ቀበሌው እንዳለውም ገልጸዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል መዘጋጀታቸውን የገለጹት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሞገስ ኃይሌ ለዚህም የሚኾን የጉድጓድ እና የችግኝ ማፍላት ሥራዎች ተጠናቅቀው ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት ከተተከሉ ችግኞች 65 በመቶ መጽደቃቸውን የገለጹት ምክትል ኀላፊው የዋግ ኽምራን የድርቅ ተጠቂነትን ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መተግበር ግዴታችን ነው ብለዋል።

በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን የማሳደግ ኀላፊነትም አለብን ብለዋል።

በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቋቋም እና በርሃማነትን ለመከላከል ሁሉም ማኀበረሰብ ተፋሰሶችን ከእንሰሳት ንክኪ በማራቅ እና ችግኞችን በመንከባከብ የዋግ ኽምራን የቀደመ ጸጋ ለመመመለስ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምሥራቅ ጎጃም ዞን የምዕራፍ ሁለት የመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተጀመረ።
Next articleየደብረብርሃን ከተማ ነዋሪዎች በወቅታዊ የሰላም ሁኔታ እየመከሩ ነው።