
ደብረ ማርቆስ: ሐምሌ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የምዕራፍ ሁለት የመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በደጀን ከተማ አሥተዳደር ግብግብ ቢዛልኝ ቀበሌ ተጀምሯል።
“የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትዉልድ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የተጀመረው።
የዚህ ዓመት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ቂም እና ቁርሾን በመንቀል አንድነትን፣ ሰላምን እና መፈቃቀርን የምናጸናበት የተከልናቸዉን ችግኞች በመንከባከብ የምናጸድቅበት ሊኾን እንደሚገባ የምሥራቅ ጎጃም ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ተናግረዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን በምእራፍ ሁለት የመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 215 ሚሊዮን ችግኝ በ21 ሺህ 600 ሄክታር መሬት አፈርና ውኃ እቀባ በተሠራባቸውና 23ሺ 452 የደን አግሮ ፎረስተሪ በተከናወነባቸው ስፍራዎች ላይ እንደሚተከል የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበበ መኮንን ተናግረዋል።
አቶ አበበ በሀገር አቀፍ በሚወጣው መርሐ ግብር መሰረት በዞኑ በአንድ ቀን ከ36 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ያነጋገርናቸው ወጣቶች እና አርሶ አደሮችም የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ ላይ በንቃት እንደሚሳተፉ ነግረውናል።
በደጀን ከተማ አሥተዳደር በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑን ጨምሮ፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና የወረዳ መሪዎች፣ ወጣቶች እና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!