
ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ እስከ አሁን ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ለመውሰድ መመዝገባቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የዲጅታል መታወቂያ አገልግሎት “አንድ ሰው አንድ ነው” የሚለውን መርህ ይዞ የግለሰቦችን መረጃ በመሰብሰብ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየተካሄደ ይገኛል።
የምዝገባ ሂደቱም እስከ አሁን በቅንጅትና በተሳለጠ መልኩ እየተከናወነ መኾኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት የተቋማት ተሳትፎ አማካሪ ኦላና አበበ፤ የዲጅታል መታወቂያ አገልግሎት ሀገራዊ ፋይዳው የላቀ መኾኑን ይናገራሉ።
የዲሞግራፊክና ባዮሜትሪክ መረጃን መዝግቦ በማዕከላዊ ቋት በመያዝ ለእያንዳንዱ ነዋሪ ልዩ ቁጥር መስጠት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በፕሮጀክቱ በቀጣይ ሦስት ዓመታት 90 ሚሊየን ዜጎችን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አስታውሰዋል።
በመኾኑም እስካሁን ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ለመውሰድ መመዝገባቸውን አቶ ኦላና ገልጸዋል።
ለሦስት አመታት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከባንኮች፣ ከገቢዎችና የወሳኝ ኩነት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት በፋይናንስ ዘርፍ መተግበር በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ግልጽነትን እና አካታችነትን በማጎልበት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል።
ኢትዮጵያ ወደ ላቀ የዲጂታል ፋይናንስ ሥነ-ምህዳር ለምታደርገው ጉዞም የላቀ ፋይዳ አለው። የተደራጀ የመታወቂያ ሥርዓት መዘርጋት በራሱ ለአገልግሎት አቅራቢዎች አስተማማኝ ማረጋገጫ መኾን እንደሚያስችልም ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!