“ጎርጎራ ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ፣ ታሪክን ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ራሱ ታሪክ የኾነ ፕሮጀክት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

99

ባሕር ዳር: ሐምሌ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በጎርጎራ ፕሮጄክት ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ የተገኙት ተሳታፊዎች አስደናቂ ሥራ በጎርጎራ ማየታቸውን ገልጸዋል። የልማት ሥራዎች በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንዲሰፉ ሰላምን በማምጣት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። በጎርጎራ የተሠራው ሥራ ኢትዮጵያን በቱሪዝም ዘርፍ በዓለም ከፍ የሚያደርግ መኾኑንም ገልጸዋል።

የጎርጎራን ሥራ ያመነጩ አዕምሮዎች እና የሠሩ እጆች ኢትዮጵያን የማስዋብ ተስፋ እና አቅም እንዳለ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል። ጎርጎራ ባሕሉን፣ ታሪኩን እና እሴቱን ሳይለቅ የተሠራ ስለመኾኑንም ተናግረዋል። ለሥራው አገልግሎት የዋለው ቁሳቁስም የአካባቢውን ሀብት የተጠቀመ መኾኑን ነው የገለጹት።

ከአማራ ሕዝብ የሚጠበቀው ከመወቃቀስ በመውጣት በአንድነት መሥራት ነው ብለዋል። መሪዎችን መደገፍ እና አብሮ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። የክልሉን የሰላም ችግር በውይይት በመፍታት የልማት ሥራዎችን ማፋጠን እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

አማራ እርስ በእርሱ ከመገዳደል ራሱን ወደ ልማት ማዞር እንደሚገባውም ገልፀዋል። የአንድ እናት ልጆች ፍቅር እንጂ መገዳደል አይበጃቸውም ነው ያሉት። ጎርጎራን ባየንበት ዓይን እና በተሰማን ደስታ ሌሎች ልማቶችን ማየት እንጂ ደም ሲፈስስ ማየት አንሻም ብለዋል። ውብ ኾነው የተሠሩ ሥራዎች ከእነ ውበታቸው እንዲዘልቁ መጠበቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ መንግሥት የልማት እና የኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዲፋጠኑ እየሠራ ነው ብለዋል። የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በከፍተኛ ወጪ መገንባቱንም አስረድተዋል። በቂ ትኩረት ያልተሰጣቸው አካባቢዎች በተለየ ትኩረት እየተሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የፌደራል መንግሥት ፕሮጄክቶችን ሠርቶ ለአማራ ክልል ማስረከቡንም አመላክተዋል።

በአማራ ክልል የሎጎ ሐይቅና የጎንደር ፋሲለደስ ቤተመንግሥት የአካባቢውን ታሪክ በሚመጥን መልኩ እየተሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል። የጎርጎራ ፕሮጀክት የአካባቢውን ታሪክ፣ ባሕል እና እሴት ታሳቢ ያደረገ ሥራ መኾኑንም ተናግረዋል። ጎርጎራ የጣና ሐይቅ እና ከሌሎች ተፈጥሯዊ ጸጋዎች ጋር በሚስማማ መንገድ እንደተሠራም ነው ያስረዱት። የጎርጎራ ፕሮጄክት የተገነባባቸው ቁሳቁስ የፋሲል አብያተ መንግሥት በተገነቡባቸው አይነት እንደኾነም አስገንዝበዋል። ጎርጎራ ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ፣ ታሪክን ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ራሱ ታሪክ የኾነ ፕሮጀክት ነው ብለዋል። ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ እድል የፈጠረ መኾኑንም አመላክተዋል።

መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ ከሚሠራው ሥራ ጎን ለጎን የልማት ሥራ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ችግር አለ ብለን የልማት ሥራዎችን አናቆምም ነው ያሉት። በአንድ በኩል ሰላምን ማጽናት በሌላ በኩል ልማትን ማፋጠን የመንግሥታችን መገለጫ ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። ለልማት ላባችንን ማፍሰስ እንጂ በግጭት ደማችንን ማፍሰስ አይገባም ነው ያሉት። የመገዳደል እና ደም የመፋሰስ ታሪክ መቆምና መቋረጥ እንደሚገባም ገልጸዋል። የጎርጎራ ፕሮጄክት መንግሥት ልማትን እያሰፋ እንደሚሄድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ማሳያ መኾኑንም አመላክተዋል። የትናንትን ታሪክ የሚያጎሉ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ትናንትናን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ አስተሳስሮ የሚተጋ መንግሥት እንዳለ መታወቅ ይገባዋልም ብለዋል።

መንግሥት አሁን ያለውን ችግር በሰላም መፍታት እንደሚፈልግም አስታውቀዋል። የሰላም ፍላጎታቸውን በተደጋጋሚ መናገራቸውንም ገልጸዋል። ግጭቱ ሳይጀመር በውይይት ብንፈታው መልካም ነበር፣ አሁንም በውይይት መፍታት ይገባናል ብለዋል። ከሰላም ጥሪ በላይ ምንድን ነው መደረግ ያለበት? ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ማኅበረሰቡ መንግሥት ማድረግ ያለበትን አድርጓል ወይስ ጎድሎታል የሚለውን ማንሰላሰል አለበት ነው ያሉት።

ክልሉን ተወዳዳሪ የሚያደርገው የልማት ሥራ መኾኑንም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ ልማቱን በመደገፍ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም አሳስበዋል። ጎርጎራ ላይ አዲስ ሃብት እንዳስቀመጥነው ሁሉ ወደፊትም የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ከጎናችን መኾን አለባችሁ ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከሕዝቡ ጋር በመኾን ያከናወናቸው ተግባራት በግጭት ውስጥም ኾኖ ውጤት ማስመዘገብ እንደሚቻል አስተምሮናል” ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ
Next articleየሀገራዊ ምክክር ሂደት የሚደናቀፍባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድናቸው?