
ደብረ ማርቆስ: ሐምሌ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳደር የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጻም ግምገማ እና የቀጣይ የክረምት ወራት ንቅናቄ መድረክ በደጀን ከተማ አካሂዷል። የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በዞኑ የተከሰተውን ግጭት ለመቀልበስ የዞኑ አሥተዳደር ከሕዝቡ ጋር በመኾን በሠራው ሰፊ ሥራ በአሥተዳደሩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ መነቃቃት እየታየ ነው ብለዋል። ያከናወናቸው ተግባራት በግጭት ውስጥም ኾኖ ውጤት ማስመዘገብ እንደሚቻል አስተምሮናል ነው ያሉት። አቶ ኑርልኝ በቀጣይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ውስጣዊ ችግሮችን ማረም እና አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።
የደባይ ጥላት ግን ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ተመሥገን ያለው እና የሰዴ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ፈንታሁን ታደሰ በወረዳቸው የታየውን አንፃራዊ ሰላም ተከትሎ በግጭት ምክንያት የተጓተቱ የልማት ተግባራት እና የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመፍታት እየሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል።
የጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ የኔዋ ደመቀ እና የደጀን ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ጌታቸው ሰውነት ያለፈውን ለማካካስ በተያዘው በጀት ዓመት በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋዬ በላይ ባላፈው አንድ ዓመት የተከሰተው ግጭት ችግሮችን በፅናት መሻገር እንደሚቻል አስተምሮናል ብለዋል።
በቀጣይም የዞኑን ሕዝብ በትጋት በማገልገል ከችግር ለማውጣት፣ ሰላሙን ለማረጋገጥ፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎቹን ለመፍታት የዞኑ መሪዎች ትልቅ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!