የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት

74

ባሕር ዳር: ሐምሌ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች የዓለም ሀገራት ሁሉ ለረጅም ዘመን በንጉሣዊ ሥርዓት ቆይታለች፡፡ በወቅቱ የነበረው አሥተዳደር ደግሞ የተጻፈ ሕገ መንግሥት አልነበረውም፡፡ በመኾኑም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የኾነውን ዘመናዊ የተጻፈ ሕገ መንግሥት ያጸደቁት በዚህ ሳምንት ነበር፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት ሲጸድቅ ንጉሡ እንዲህ ብለውም ነበር፡፡ “…ሕግ ለሰው ከሁሉ ነገር የበለጠ የሚጠቅም መኾኑን ማንም አይስተውም። መከበርም መጠቀምም የሚገኙት በሕግ ነው። መዋረድም መጎዳትም የሚመጡት በሕግ መጓደል የተነሳ ነው።ግፍ እና በደልም የሚበዙት ሕግ ባለመቆሙ ነው” ማለታቸው በታሪክ ይጠቀስላቸዋል። በንጉሣዊ ሥርዓቱ ዘመን አንድ ፍርድ ተጓደለ ያለ ሰው “በሕግ አምላክ!” ሲል በተጻራሪ የቆመ ሰው “በጄ” ብሎ ራሱን ለሕግ ያስገዛ ነበር፡፡ ቀደምት አባቶች እንደሚሉት “በሕግ አምላክ!” ሲባል ወደታች የሚወርድ የወንዝ ውኃ እንኳ ይቆም እንደነበር እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። አባባሉ ግነት እንዳለው ግልጽ ነው፤ ነገር ግን የሕግን ኃያልነት ለመግለጽ የተጠቀሙበት መኾኑን ልብ ይሏል፡፡ በዚህ እሳቤ ውስጥ ነው የመጀመሪያው ዘመናዊ የተጻፈ ሕገ መንግሥት የጸደቀው፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት የተረቀቀው በንጉሡ ቀጥተኛ ትእዛዝ እንደኾነ ይነገራል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ሀገሪቷ ተራማጅ እና ሥልጡን መኾኗን ለዓለም ሕዝብ ለማሳተዋወቅ ነው። ይህን ሕገ መንግሥት ያረቀቁት ደግሞ በሩሲያ የተማሩ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ነበሩ። ደጃዝማች ተክለሐዋሪያት ሕገ መንግሥቱን ለማርቀቅ አጼ ኃይለሥላሴ በቀጥታ ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው ስለ ግለ ሕይዎት በጻፉት መጽሐፍ ላይ አስፍረዋል።

ደጃዝማች ተክለሐዋሪያት ሕገ መንግሥቱን ቢያረቅቁትም ከሚኒስትሮች እና የክፍለ ሀገር መኳንንቶች የተውጣጣ 11 አባላት ያሉት የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚቴ ተቋቆሞ ነበር። ኮሚቴው የእንግሊዝና የጃፓን ሕገ መንግሥቶች ተተርጉመው ቀርበውለት ተወያይቶበት እና በቀጥታ ወደ ንጉሡ ተልኮ ነው የጸደቀው።

ንጉሡ ሕገ መንግሥቱን ከማጽደቃቸው በፊት ብላቴን ጌታ ሕሩይ እና ራስ ካሳ ከሚባሉ አማካሪዎቻቸው ጋር እንደመከሩበትም ይነገራል፡፡ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሕገ መንግሥት ለዘውዳዊ ሥርዓቱ ያደላ ቢኾንም ያመጣቸው ለውጦችም በታሪክ በበጎ ተጽፈውለታል።ለምሳሌ ማንኛውም መሳፍንት በግሉ ከውጭ ሀገራት ጋር በመጻጻፍ የጦር መሣሪያ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን መቀበል አይችልም የሚለው ይጠቀሳል።

ይህ በሐምሌ ወር 1923 ዓ.ም የጸደቀው ሕገ መንግሥት ሁለት ምክር ቤቶችንም አቋቁሟል። ምክር ቤቶቹም የሕግ መወሰኛ እና የሕግ መምሪያ ምክር ቤት የሚባሉ ናቸው። በመረጃ ምንጭነት አዲስ ዘመን ጋዜጣን እና “የኢትዮጵያ ታሪክ” መጽሐፍን ተጠቅመናል፡፡
👉 የቅርሶች መመለስ
አፍሪካን በዋናነት እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቀራመት ካሰፈሰፉት የአውሮፓ ሀገራት መካከል አንዷ እንግሊዝ ናት፡፡ ሀገሪቱ ሌሎችን በቅኝ ግዛት እንደያዘችው ሁሉ ኢትዮጵያንም ለመያዝ ቋመጠች፡፡ እቅዷን ለማሳካትም በጄኔራል ናፒዬር የሚመራ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ላከች፡፡

ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀው ግዙፍ ጦር እንዳሰበው ኢትዮጵያን ማንበርከክ አልቻለም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያውያን እናት እና አባት አርበኞች ድባቅ መቱት፡፡ ባሕር ተሻግሮ የመጣው የእንግሊዝ ጦር ገና ከሀገሩ ሲነሳ ኢትዮጵያን በቅኝ ከመግዛት ባለፈ ሌላ ያሰበው ሴራ እንደነበረው ለማሰብ አይከብድም፡፡”ለምን?” ቢሉ ከጦር ጋር ሪቻርድ ሆምስ የተባለ የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ አብሮ መጥቷልና፡፡ ይህ የኾነው የቅርስ ዘረፋውን በባለሙያ ለመምረጥ እንዲመቸው በማሰብ ነው፡፡

እንግሊዝ አንደኛውን በቅኝ የመግዛት ዓለማውን ማሳካት ስላልቻለ ወደ ዘረፋ ተሸጋገረ፡፡ እንደማሳያም እጄን አልሰጥም ካሉት አፍሪካዊ ንጉሥ አስክሬን ላይ (አጼ ቴዎድሮስ ላይ ) የአንገት መስቀል እና የጣት ቀለበታቸውን፣ ሸሚዛቸውን እና ሽጉጣቸውን ከመዝረፋቸውም ባሻገር ሹሩባቸውን ሳይቀር ሸልተው ወሰዱ፡፡ በጠቅላላው በ15 ዝሆኖች እና በ200 በቅሎዎች የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ እንግሊዝ ተጋዙ፡፡ ታላላቅ የውጭ ሀገራት የመገናኛ ተቋማት እንግሊዝ በኢትዮጵያ መሸነፏን ሲገልጹ ” የእንግሊዝ ጦር ኢትዮጵያውያን በጦርነት መርታት ቢሳነው ቅርስ ዘርፎ ተመለሰ” በማለት ተሳልቀውባቸዋል፡፡ ይህን ዜና ተከትሎም ኢትዮጵያውያን ታሪክ ጸሐፊዎች “ከዚያ በፊት ነጻ ሕዝብ እንደነበርን ዛሬም ነጻ ሕዝብ ነን ” በማለት ገልጸውታል፡፡

ኢትዮጵያውያን እያደሩም በእንግሊዞች የተዘረፉባቸውን ቅርሶች እንዲመለስላቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ቅርሶች እንዲመለሱ በተከታታይ እና ያለመታከት ሙግትም ተደረገ፡፡ ይህ ጉዳይ ሲበረታ እንግሊዞች ዘርፈው የወሰዷቸውን ቅርሶች “በውሰት ልስጣችሁ” እስከማለት ደረሰች፡፡

በኢትዮጵያ በኩል በተደረገ ጠንካራ ጥረት የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ወደ ሀገሩ ማስመለስ መቻሉን ልብ ይሏል፡፡ የኾነ ኾኖ ኢትዮጵያውያን በብርቱ ትጋታቸው ቅርሱ እንዲመለስ መግባባት ላይ ደረሱ፡፡
የእንግሊዝ መንግሥት ሚኒስትር ቻርልስ ቤንቲንክም ዘውዱን በሠረገላ አጅበው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ተሰማ። ግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱ እና ልዑል አልጋ ወራሽ በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ በተለይ በተሰናዳው ሥፍራ ከመኳንንት ጋር ተቀምጠው ይጠብቁም ነበር። የግቢ ዘበኞችም በቀኝ እና በግራ በኩል ተሰልፈው ነበርና የእንግሊዝ ሠረገላ በሰልፉ መካከል አልፎ ከመንግሥት ፊት ደረሰ። ለክብሩ በተዘጋጀው ጠረጴዛ ላይ ሚስተር ቤንቲንክ ዘውዱን ከሠረገላው አውርደው ጠረጴዛው ላይ አስቀመጡትና ከዚህ ቀጥሎ ያለውን መልዕክት ተናገሩ፡፡

“ግርማዊት ሆይ! በንግሥት ቪክቶሪያ መንግሥት በ1860 ዓ.ም ከመቅደላ የተወሰደውን የአጼ ቴዎድሮስን ዘውድ የታላቂቱ ብሪታንያ እና የአየርላንድ፣ ከባሕር ማዶ ያሉት ግዛቶች ንጉሥ እና የሕንድ ንጉሠ ነገሥት በኾኑት በግርማዊ ጌታዬ በንጉሡ ትዕዛዝ ለግርማዊት ንግሥት በማክበር መለስን ” ብለዋል፡፡ ታዲያ ይህ የኾነው ሐምሌ አራት ቀን 1917 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር። በመረጃ ምንጭነት “የሐያኛ ክፍለ ዘመን መባቻ” መጽሐፍን መጠቀማችንን ልብ ይሏል፡፡
👉 አፖሎ 11
አፖሎ 11 የመንኮራኩር መጠሪያ ሥም ነው፡፡ ይህ መንኮራኮር ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎችን ይዞ ወደ ጨረቃ መጥቋል፡፡ ታዲያ ይህ ጉዞ የተዘጋጀው በአሜሪካው የጠፈር ተቋም ናሳ ነው።

መንኮራኩር ወደ ጨረቃ ሲመጥቅ ኒል አርምስትሮንግ፣ በዝ አልድሪን እና ማይክል ኮሊንስንን በመያዝ ነበር።
መንኮራኩሩ ሰዎችን ይዞ ጨረቃ ላይ ሲያርፍ የመጀመሪያ ኾኖ በታሪክ ተመዝግቧል።

ኒል አርምስትሮንግ ጨረቃ ላይ እንዳረፈም ከአፉ የወጣው የመጀመሪያው ንግግር “ይህ ለአንድ ሰው ትንሽ እርምጃ ሲኾን ለመላው የሰው ልጆች ግን ታላቅ ዕድገት (መመንጠቅ) ነው” የሚል ነበር። ይህ ሰናይ ድርጊት ፕሬዚደንት ኬኔዲ “የሰው ልጅን ጨረቃ ላይ አሳርፎ በሰላም ለመመለስ” የሰነቁትን የተቀደሰ ዓላማ ያሳካ ነበር።

አፖሎ 11 ወደ ጠፈር ሲመጥቅ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቴሌቪዥን ተመልክተውታል ሲል ዎርልድ ስፔስ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡ ይህን አፖሎ 11ን ይዞ የመጠቀው ሮኬት ፍም ጉማጅ እየተንቀለቀለ ወደ ሰማይ ሲጓዝ ያየን የዓለም ሕዝብ አጃኢብ ያስባለው በዚህ ሳምንት ሐምሌ ስድስት 1961 ዓ.ም ነበር።

#ሳምንቱንበታሪክ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብልጽግና ፓርቲ የ2016 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው።
Next article“ከሕዝቡ ጋር በመኾን ያከናወናቸው ተግባራት በግጭት ውስጥም ኾኖ ውጤት ማስመዘገብ እንደሚቻል አስተምሮናል” ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ