“በተመረቅንበት የትምህርት መስክ ሥራ ፈጣሪ በመኾን ሀገርን የሚጠቅም ሥራ እንሠራለን” ተመራቂዎች

48

ደሴ: ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኮምቦልቻ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በዲግሪ እና በደረጃ መርሐ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 736 ተማሪዎች አስመርቋል።

ተመራቂ ተማሪዎች የኮሮና ወረርሽኝ እና የሰሜኑ ጦርነት በትምህርታቸው ላይ እንቅፋት ፈጥሮ እንደነበር ጠቅሰው የተለያዩ መሰናክሎችን አልፈው በመመረቃቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ተመራቂዎች “በቀጣይም በተመረቅንበት የትምህርት መስክ ሥራ ፈጣሪ በመኾን ሀገርን የሚጠቅም ሥራ እንሠራለን” ብለዋል።

የኮምቦልቻ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ተወካይ ዲን ሰለሞን ነጋሽ ለተመራቂ ተማሪዎች እና ለተማሪ ወላጆች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት ያገኙትን ዕውቀት፣ ክህሎት እና ሥነ ምግባር መሬት ላይ በማውረድ ሀገራቸውን የሚጠቅም ሥራ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።

“የኮሌጁ የመጨረሻ ግብ ተማሪዎች በተመረቁበት የትምህርት መስክ የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ ማድረግ መኾኑንም” ገልጸዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድ አሚን የሱፍ የሥራ ፈጠራ ክህሎት ላላቸው እና በፈጠራ ሥራ ላይ መሰማራት ለሚሹ ተመራቂ ተማሪዎች ከተማ አሥተዳደሩ የመሥሪያ ሼዶችን ገንብቶ እንደሚያስረክብ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋራ በመኾን የመሥሪያ ካፒታል ብድር እንዲያገኙ እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ መስዑድ ጀማል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መንግሥት እና ታጥቀው ጫካ የገቡ ወገኖች የሰላም ካውንስሉ ያቀረበውን ጥሪ የመቀበል ታሪካዊ ኀላፊነት አለባቸው” የደሴ ከተማ ነዋሪዎች
Next article“የሕዝባችንን ፍላጎት ለማሟላት በየትኛዉም ጊዜ እና አጋጣሚ ችግሮቻችን በውይይትና በድርድር እንድንፈታ በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ አድርገናል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ