“መንግሥት እና ታጥቀው ጫካ የገቡ ወገኖች የሰላም ካውንስሉ ያቀረበውን ጥሪ የመቀበል ታሪካዊ ኀላፊነት አለባቸው” የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

26

ደሴ: ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” የደሴ ከተማ የሰላም ውይይት መድረክ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በውይይቱ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ መክፈቻ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ሕዝቡን ለበርካታ ፈተናዎች ያጋለጠ መኾኑን ጠቁመዋል።

ግጭቱ ተመሳሳይ ጥያቄ ያላቸው ወንድማማቾች በእርስ በእርስ ግጭት እንዲገዳደሉ፣ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ እንዳይመለሱ እና እንዲወሳሰቡ አድርጓል ያሉት አቶ ሳሙኤል ግጭቱ የክልሉን ሰላም መኾን ለማይፈልጉ ኃይሎች በር ከፍቷል ብለዋል።

በመኾኑም ክልሉ ከግጭት ወጥቶ ወደተረጋጋ ሰላም እንዲገባ የሚያስችሉ የሰላም ኮንፈረንሶች በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተካሂደዋል ነው ያሉት።

የአሁኑ መድረክ በከተማ አስተዳደር ደረጃ የማጠቃለያ ውይይት መኾኑን ጠቅሰው ማኅበረሰቡ በየመድረኮቹ ሰላምን እንደሚሻ አጥብቆ ጠይቋል ብለዋል።

ነዋሪዎች ለራሳችን ስንል ለሰላም እና ለአንድነት እንሰራለን ማለታቸውን ገልጸው፤ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል እና የሃይማኖት አባቶች ለሰላም በርትተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው በየመድረኩ ሃሳብ እንደተሰነዘረም ነው የተናገሩት።

የክልሉን ሰላም ዘላቂ እና አስተማማኝ ለማድረግ የተጀመሩ የሰላም ጥሪዎችን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተግባራዊ በማድረግ የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በበኩላቸው በየአካባቢያቸው ስለሰላም ተከታታይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው በክልሉ በሰላም እጦት ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ማጋጠማቸውን ተናግረዋል።

በመኾኑም ክልሉ ከዚህ በላይ በግጭት ውስጥ መቆየት የለበትም ያሉት ተወያዮቹ “መንግሥት እና ታጥቀው ጫካ የገቡ ወገኖች የሰላም ካውንስሉ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ምክክር እና ውይይት በመምጣት የክልሉን ሰላም የማረጋገጥ ታሪካዊ ኀላፊነት አለባቸው” ብለዋል።
ተወያዮቹ የከተማዋን ብሎም የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ እንደዜጋ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውንም አረጋግጠዋል።

ውይይቱ ባለ 9 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል

ዘጋቢ፦ከድር አሊ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ለመንግሥት ሠራተኞች ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ፡፡
Next article“በተመረቅንበት የትምህርት መስክ ሥራ ፈጣሪ በመኾን ሀገርን የሚጠቅም ሥራ እንሠራለን” ተመራቂዎች