“እኛ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተፋላሚ ኀይሎች ሰላም ፈጥረው ሕዝቡ እፎይታ እንዲያገኝ እንሠራለን” የጠለምት ወረዳ የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች

28

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ፋኖም ኾነ መከላከያ ሁሉም ልጆቻችን ናቸው፤ እኛ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተፋላሚ ኀይሎች ሰላም ፈጥረው ሕዝቡ እፎይታ እንዲያገኝ እንሠራለን” የጠለምት ወረዳ የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች
በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡

የኮንፈረንሱ ተሳታፊ ቄስ ጌቴ ደሴ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ወንድም ወንድሙን የሚገድልበት ችግር ውስጥ ገብተናል ብለዋል፡፡ “ተፋላሚ ሃይሎች ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት በኀይል ሞክረዋል፤ ዘላቂ ግን አይኾንም” ያሉት ቄስ ጌቴ ዘላቂ የሚኾነው በመነጋገር እና በመመካከር ሲኾን ነው ብለዋል። ችግሩን በሰላም ለመፍታት በሚደረገው ጥረት እኔም የድርሻየን እወጣለሁ ብለዋል፡፡

ሌላኛው የኮንፈረንሱ ተሳታፊ አቶ ንጉሱ ተረፈ በበኩላቸው ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የሰላምን አስፈላጊነት እየመከርን ነው ብለዋል፡፡ “ፋኖም ኾነ መከላከያ ሁሉም ልጆቻችን ናቸው፤ እኛ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተፋላሚ ሃይሎች ሰላም ፈጥረው ሕዝቡ እፎይታ እንዲያገኝ እንሠራለን” ብለዋል፡፡

በጠለምት ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኃይለገብርኤል ምኅረቴ የሰላም ኮንፈረንሱ ከቀበሌ ጀምሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸው እየተፈጠረ ያለውን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ በሰላም ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ከወረዳው ሁሉም የገጠር እና ከተማ ቀበሌዎች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች እና ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በልዩ ልዩ የትምህርት አይነቶች ያሰለጠናቸውን 885 ተማሪዎች አስመረቀ።
Next articleበአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት የተለያዩ ሹመቶችን ሰጠ።