
ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት እና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ ዳይሬክተር ወንድሜነህ ልየው እንዳሉት ሥርዓተ ምግብ የማኅበረሰቡ የጤና ችግር እንዳይኾን ከተነደፉ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም ነው።
ፕሮግራሙ አሁን ላይ በድርቅ የተጎዱ እና በምርታማነታቸው ዝቅተኛ በኾኑ 86 አካባቢዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። እስከ አሁን የዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት ተደራሽ ባልኾነባቸው 24 ወረዳዎች ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት 794 ኩንታል አልሚ ምግብ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል። ድጋፉ ለችግር ተጋላጭ ለኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚውል እንደኾነም ተገልጿል።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም የጤና እና ሥርዓተ ምግብ አማካሪ መንበሩ ሞላ ፕሮግራሙ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2030 በክልሉ መቀንጨርን ዜሮ ለማድረስ የተቋቋመ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህ ወቅትም በክልሉ ድርቅ በተከሰተባቸው 24 ወረዳዎች በሕጻናት እና እናቶች ሥርዓተ ምግብ ላይ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት። በቀጣይም የሕጻናትን እና የእናቶችን የአመጋገብ ችግር በዘላቂነት ሊፈቱ በሚችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!