የታጠቁ ኀይሎች ለውይይት እንዲቀርቡ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

15

ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫና እያሳደረባቸው መኾኑን የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች አንስተዋል። በሰላም መደፍረሱ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች፣ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት መቋረጣቸውንም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

የታጠቁ ኀይሎች ጥያቄዎቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ በሰላም ካውንስሉ የቀረበው የመፍትሔ አማራጭ የሚደነቅ መኾኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ የሰላም አማራጩን በመቀበል የክልሉን ሕዝብ የሰላም እና የልማት ባለቤት ማድረግ አለባቸው ብለዋል። “ከገባንበት የእርስ በእርስ ግጭት ወጥተን ወደ ልማት መመለሱ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው” ያሉት ተሳታፊዎቹ “የታጠቁ ኀይሎች ለውይይት እንዲቀርቡ የበኩላችንን ሚና እንወጣለን” ብለዋል።

በተለይም በዞኑ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈጸመ ያለው ልዩ ልዩ ወንጀል ዛሬም ድረስ እልባት አለማግኘቱን ተሳታፊዎቹ አንስተዋል። በዚህም የዞኑ ማኅበረሰብ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ እና ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ እንዲቋረጥ ማድረጉንም ተናግረዋል። በመኾኑም መንግሥት ከሕዝብ ጎን በመኾን ሕግን ማስከበር እና የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ ይገባል ብለዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና የልማት ተግባራትን ለማስቀጠል ከተፈለገ ሁሉም በእኔ ባይነት ስሜት ለሰላም አበክሮ መሥራት እንዳለበት የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱከሪም ሙሐመድ ተናግረዋል። መንግሥት ከሕዝብ ጎን በመኾን ሕግ የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ከንቲባው ጫካ የገቡ ወገኖች ለውይይት እንዲቀርቡ ኅብረተሰቡ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ የማንነት እና የወሰን አሥተዳደር ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በክልሉ እና በፌዴራሉ መንግሥት እየተሠራ ስለመኾኑም ከንቲባው ተናግረዋል። በኮንፈረንሱ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶ አደሮች እና ሌሎችም የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀሉም አካል በመወያየት ክልላችን የሰላም አየር እንዲተነፍስ ማድረግ ይገባዋል” የኮምቦልቻ ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች
Next articleየሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአልሚ ምግብ ድጋፍ አደረገ።