
ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በኾኑ የሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በሚቀጥሉት 10 ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በኾኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ እየተጠናከረ እንደሚሄድ ገልጿል። የሚጠበቀው እርጥበት የመካከለኛ ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራት፣ በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎች የውኃ ፍላጎትን ለማሟላት እንደሚረዳ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ነው ያስታወቀው።
በዚሁ ወቅት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛው እና በሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ ስፍራዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅም ነው የገለጸው። በአማራ፣ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ በአፋር፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ አመላክቷል፡፡
በዚሁ የክረምት ወቅት የሚኖረው እርጥበት የሰብሎችን የውኃ ፍላጎት ለማሟላት፣ የግብርና ተግባራትን ለማከናወን፣ ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ለግጦሽ ሳር ልምላሜም አዎንታዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስታውቋል። በተፋሰሶች ያለውን የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር የውኃ ሃብትን ከማሻሻል እና የግድቦችን እና የወንዞችን የውኃ መጠን ከማሳደግ አንጻር አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚኖረው ከባድ ዝናብ በማሳዎች ላይ የውኃ መተኛት፣ የአረም መስፋፋት ሊከሰት እንደሚችልም አመልክቷል። በተጨማሪም ከእርጥበት ጋር የተያያዙ የሰብል በሽታዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ቅድመ ዝግጀት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ የሚኖረው ዝናብ ከሚኖረው ጠቀሜታ ባሻገር ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኢንስቲትዩቱ ማሳሰቡን ኢቢሲ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!