
ሁመራ: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሐምሌ 5 የዝክረ ሰማዕታት መታሰቢያ ቀን በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁመራ ከተማ “በደም የፈካ ነጻነት፤ እስከ ሞት የታመነ አማራነት” በሚል መሪ መልእክት ተከብሯል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ በሕወሃት የሥልጣን ዘመን በቋንቋው እንዳይናገር፣ ባሕል እና እሴቱን እንዳያስቀጥል ብሎም አማራ ነኝ ብሎ እንዳይናገር ግፍ እና መከራ ሲፈጽምበት እንደነበር አስታውሰዋል።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ በአባቶቹ ርስት ባለመደራደር ከፋኝ ብሎ በመደራጀት በዱር በገደሉ ለማንነቱ ሲታገል መቆየቱንም አንስተዋል። ሐምሌ 5/ 2008 ዓ.ም የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ የነጻነት ችቦ በኮሎኔል ደመቀ አማካኝነት እንደተለኮሰ ገልጸዋል።
በርካቶች ለወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውን የገለጹት አቶ አሸተ ጀግኖችን በመዘከር ፈለጋቸውን ልንከተል ይገባል ብለዋል። ሐምሌ 5 የአማራ ሕዝብ የነጻነት ቀን ነው ያሉት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ናቸው።
ኮሎኔል ደመቀ በዓሉ ለነጻነት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች የሚዘከሩበት መኾኑን ገልጸዋው ወጣቶች የማንነት ጥያቄው ሕጋዊ ዕውቅና እንዲያገኝ የበኩላቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ አደራ የሰጠንበት ቀን ነው ብለዋል። የማንነት ጥያቄው ሕጋዊ ዕውቅና እንዲያገኝ አንድነትን በማጠናከር እና መከፋፈልን በማስወገን በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የበዓሉ ታዳሚ የሁመራ ከተማ ወጣቶች በበኩላቸው ከነጻነት ማግስት ባሕላዊ ልብሳቸውን በመልበስ እና በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በመናገር በነጻነት እያከበሩ መኾኑን ተናግረዋል። ለነጻነት ዋጋ የከፈሉ ሰማዕታትን አመሥግነው የሰማዕታት አደራን በመቀበል ነጻነታቸውን አስጠብቆ ለመዝለቅ ከዞኑ አመራር ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አስተያየታቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!