
መተማ: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ አሥተዳደር “ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
በወረዳው በግድያ፣ እገታ እና ዘረፋ ወንጀል የተሰማሩ የግል ጥቅመኞች መበራከታቸውን የገለጹት ተሳታፊዎቹ እነዚህ ኀይሎች የዞኑን ማኀበረሰብ ረፍት በመንሳት የሰላሙ እና የልማቱ ተጠቃሚ እንዳይኾንም እየሠሩ ነው ብለዋል። በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት እንደአጋጣሚ በመጠቀም የሕዝቡን አንድነት እና አብሮነት ለመሸርሸር የሚጥሩ ኀይሎች መኖራቸውንም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ይመለሥ ብለው ጫካ የገቡ ኀይሎች ጥያቄዎቻቸውን በሠለጠነ እና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በሰላም ካውንስሉ የቀረበው አማራጭ የሚደነቅ መኾኑን ተሳታፊዎቹ አንስተዋል። መንግሥትም ከታጠቁ ኀይሎች ጋር ለመደራደር እና ለመወያየት ፈቃደኛ መኾኑ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
መንግሥት እና የታጠቁ ኀይሎች ለሚያደርጉት ድርድር እና ውይይት የድርሻችውን እንደሚወጡ ተሳታፊዎች አረጋግጠዋል። የመተማ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግዛት ሰረጸ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በመንግሥት ብቻ ሳይኾን በኅብረተሰቡ ተሳትፎ መኾኑን በመረዳት ሁሉም ለሰላሙ ዘብ ሊቆም እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን ሊያረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሁሉም ጥያቄ ነው ያሉት የመተማ ወረዳ አሥተዳዳሪ ደሳለኝ ሞገስ ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ነፍጥ አንግበው የወጡ ኀይሎችን ማስገንዘብ ይገባን ብለዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ፈንታሁን ቢኾነኝ በበኩላቸው ጥያቄ አለን ብለው ጫካ የገቡ ኀይሎች በሰላም ካውንሰሉ የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች የኀብረተሰብ ክፍሎች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በወረዳው የግድያ፣ እገታ እና ዘረፋ ወንጀል እየተፈጸመ መኾኑን ያረጋገጡት ኀላፊዎቹ ለጋራ ሰላም እና ደኅንነት ሲባል ኅብረተሰቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመሰለፍ የእነዚህን ኀይሎች የጥፋት ተግባር ሊያስቆም ይገባን ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!