
ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የሰሜን ጎጃም ዞን የመንግሥት ሠራተኞች የሰላም ውይይት ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን በአማራ ክልል የተከሰተው የሰላም እጦት በዞኑ ሰብዓዊ፣ ማኀበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። ዋና አሥተዳዳሪው ስለደረሰው ጉዳት አብነት ሲያነሱም በዞኑ የሚገኙ 502 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ከርመዋል። ስለኾነም 400ሺህ 998 ተማሪዎች ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት በ2016 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ውድ የአንድ ዓመት የትምህርት ጊዜ ባክኗል ብለዋል።
ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎችም በጸጥታ ችግር ግብዓት ማግኘት ስላልቻሉ በሙሉ አቅማቸው ለኀብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ነው ያሉት። በዞኑ ከአዴት- ሰከላ- ፈረስ ቤት በ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር 62 ኪሎ ሜትር የአሰፋልት መንገድ እየተገነባ እንደነበር የተናገሩት አቶ አሰፋ ከዱር ቤቴ_ሻውራ_ ደለጎም 260 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ በ5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እየተገነባ አንደነበር ተናግረዋል።
ይህ መንገድ ሲጠናቀቅም ክልሉን በመተማ በኩል ከሱዳን ጋር የሚያገናኝ ስለኾነ ይዞት የሚመጣው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን በከልሉ አስተማማኝ ሰላም ባለመኖሩ መንገዶቹ አንድ ዓመት ሙሉ ከሥራ ውጭ ኾነው ከርመዋል ነው ያሉት። መንገዶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ቢጠናቀቁ የክልሉን እንዲሁም የኢትዮጵያን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ይችሉ ነበር ። ይሁን እና ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘላቸው የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በጸጥታ ችግር ምክንያት ግንባታቸው በመቋረጡ በዞኑ እየደረሰ ያለውን ምጣኔ ሃብታዊ ኪሳራ ዘርፈ ብዙ መኾኑን ዋና አሥተዳዳሪው ምሳሌ ጠቅሰው ነው ያብራሩት።
ነፍጥ ያነሱ ወንድም እህቶች በጦርነት የሚመጣ ሰላም አለመኖሩን መረዳት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ “በመንግሥት በኩል በየትኛውም ሥፍራ ለመነጋገር ዝግጁ ነው” ሲሉ አቶ አሰፋ ተናግረዋል። የሰሜን ጎጃም ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ገብረሥላሴ ባዘዘው “በዞኑ የሰላም እጦቱ ያልጎዳው የኀብረተሰብ ክፍል የለም፤ ሰላም በመጥፋቱ በዞኑ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ዓመት ሙሉ ተዘግተው በመክረማቸው የደረሰው ኪሳራ በጣም ከፍተኛ ነው፤ በመኾኑም ከአጉል ጀብደኝነት በመውጣት፣ የሃሳብ የበላይነትን አምኖ በመቀበል እና የኀብረተሰብን ጥቅም ለማስጠበቅ ችግርን በውይይት መፍታት ተገቢም አስፈላጊም ነው” ብለዋል። በየአካባቢው እየተካሄደ ያለው የሰላም ውይይትም ዓላማ ይኸው ነው ሲሉ ኀላፊው ተናግረዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ፋሲካ ጌታቸው “ሰላም በመጥፋቱ ሰርተን መግባት፣ ነግደን ማትረፍ፣ ልጆቻችንን ማስተማር አልቻልንም” ነው ያሉት። በመኾኑም መሳሪያ ታጥቀው ጫካ የገቡት እና መንግሥት ወደ ሰላም ቢመጡ ትርፉ ለሕዝብ እና ለሀገር ነው ብለዋል። ወይዘሮ ፋሲካ ላቀ ሰላም ከራስ ይጀምራልና የመንግሥት ሠራተኞች ቤተሰብን፣ ጎረቤትን እና ማኀበረሰቡን ስለሰላም ጠቀሜታ ማስተማር ይገባል በማለት ገልጸዋል።
ወይዘሮ ፋሲካ ሰላም ስለደፈረሰ በሰሜን ጎጃም ዞን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በመታወካቸው የተጎዳው ሕዝብ እፎይ የሚለው ነፍጥ አንስተው እየተዋጉ ያሉ አካላት ወደ ሰላም ሲመጡ ነው ብለዋል። የቀረበው የሰላም ጥሪ ተገቢ መኾኑንም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!