“ሥርጭቱ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ለመከላከል በክልሉ ግብረ ኀይል ተቋቁሞ እየተሠራ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

31

ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና ክልላዊ የወባ በሽታ መከላከል ግብረ ኀይል ሰብሳቢ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) መግለጫ ሰጥተዋል።
ባለፉት አስር ዓመታት የወባ በሽታን ለመከላከል ጥረት ቢደረግም በሽታው አሁንም ድረስ የማኅበረሰብ የጤና ችግር እየኾነ መምጣቱን ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሽታው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል ብለዋል። በአንድ ሳምንት ብቻ ባልተለመደ ሁኔታ ከ53 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች የወባ በሽታ ተጠቂ መኾናቸው የሥርጭቱን ስፋት እንደሚያሳይም ተናግረዋል። በክልሉ ምዕራባዊ ክፍል በሚገኙ 34 ወረዳዎች በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ተሰራጭቶ ይገኛል ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት መቀነስ፣ የአጎበር በወቅቱ አለመቅረብ እና በአግባቡ አለመጠቀም፣ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ቦታዎችን ለይቶ የቁጥጥር ሥራ አለመሥራት፣ በበጋ ወቅት ለመስኖ ልማት ያገለገሉ ግድቦችን በአግባቡ አለማፋሰስ እንዲሁም የተፈጠረው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ለሥርጭቱ መስፋፋት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

ክልላዊ የወባ በሽታ መከላከል ግብረ ኀይል ሰብሳቢ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) አሁን ላይ በአማራ ክልል ደረጃ ግብረ ኀይል ተቋቁሞ ሁሉን አቀፍ የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። የአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት ከፍተኛ ሥርጭት ባለባቸው 21 ወረዳዎች የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ይገኛል።

በግዥ ሂደት ላይ የሚገኘው የኬሚካል አቅርቦት ለክልሉ እንደደረሰ ርጭት የሚካሄድ ይኾናል ነው ያሉት። ለ10 ወረዳዎች የአልጋ አጎበር ለማሰራጨት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በክልሉ የቀረበውን መድኃኒት ወደ ጤና ተቋማት የማዳረስ ችግር መኖሩን ያነሱት ዳይሬክተሩ የጤና ግብዓት የጫኑ ተሽከርካሪዎች ግብዓትን ወደ ጤና ተቋማት እንዲያደርሱ ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ወረዳዎች በጀት በመመደብ ጭምር የተከሰተውን የወባ በሽታ መከላከል ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ጠይቀዋል። የጤና ባለሙያዎች ማኅበረሰቡን በማስተባበር ለወባ ትንኝ መራቢያ የኾኑ ቦታዎችን እንዳይመቹ በማድረግ እና የቀረበውን መድኃኒት በፍትሐዊነት ለማኅበረሰቡ በማድረስ የወባ በሽታን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ እንዲሠሩ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሁልጊዜም ስለ ሰላም ልንሠራ ይገባል” የሀራ ከተማ የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች
Next articleእየደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ጉዳት ለማስቀረት በውይይት ሰላም እንዲሰፍን የሰሜን ጎጃም ዞን የመንግሥት ሠራተኞች ጠየቁ።