
ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀራ ከተማ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም በሚል መሪ መልዕክት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር የማጠቃለያ ውይይት ተካሂዷል። በውይይት መድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች ተሳትፈዋል።
ተሳታፊዎቹ ስለ ሰላም አስፈላጊነት በማንሳት የሰላም ካውንስሉ ጥሪ በውጤት እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አስረድተዋል።
ከጦርነት ሞት እና የንብረት ውድመት፣ የኑሮ ውድነት እና መፈናቀል እንጂ ውጤት አላየንበትም ያሉት ተሳታፊዎቹ አሁንም ሳይረፍድ ሁሉም ኀይሎች በሰላማዊ ንግግር ችግሩን እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ የቀረበው የሰላም ውይይት የዘገየ ቢኾንም አሁንም ነገሮች ይበልጥ ሳይወሳሰቡ ለሰላማዊ ንግግሩ ተግባራዊነት ከልብ እንደሚያግዙ ነው ያብራሩት።
በከተማ አሥተዳደሩ በገለልተኛ አካላት የሰላም ካውንስል ተመርጦ 10 ነጥብ ያለው የአቋም መግለጫ ስለማዘጋጀቱም ነው የተገለጸው። በኮንፈረንሱ የማጠቃለያ ሃሳብ የሰጡት የሀራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሐመድ ሰዒድ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመኾኑ ሁሉም ለሰላም በቅንጅት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
መንግሥት ኅብረተሰቡን በማስተባበር በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት በማስቀጠል በሕዝብ የሚነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በየደረጃው ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሠራ ስለመኾኑ ከሀራ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!