በበጀት ዓመቱ 14 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።

19

አዲስ አበባ: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በበጀት ዓመቱ የተሰጡ አገልግሎቶችን በተመለከተ ለብዙኃን መገናኛ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት አገልግሎቱ ያለአግባብ ይባክን የነበረውን ሃብት በትክክል በመሠብሠብ ገቢውን በሦስት እጥፍ በማሳደግ በበጀት ዓመቱ 14 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቀዋል። ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ውሳኔዎች እግድ ላይ የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ ግለሰቦችን ነጻ ማድረግ ስለመቻሉ አስረድተዋል።

ከ34 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የውጭ ሀገር ዜጎች ጊዜያዊ እና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል። ከ51 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፓስፖርት መሰጠት መቻሉን እና ከዚህ ውስጥም 65 በመቶ በአዲስ አበባ እንደኾነ ተናግረዋል። ብልሹ አሠራርን ከማስተካከል አኳያ ከ244 በላይ ለሚኾኑ ሠራተኞች እና ደላሎች ላይ የሕግ ማስከበር ሥራ መሠራቱን አንስተዋል።

የማኑዋል አሠራርን ለማስቀረት በዲጂታል አሠራር አገልግሎቶችን በኦንላይን አፕሊኬሽን መሰጠት መጀመሩንም ገልጸዋል። ምቹ የሥራ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ የቢሮ አደረጃጀቶችን በማስተካከል እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀው አዲስ አዋጅ የዋጋ ተመን መሠረት ከነሐሴ 1/ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚኾን በተሰጠው መግለጫ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እኛም ፍላጎታችን እርቅ እንዲደረግ ነው፣ እርቅ ቢደረግ ከሰቀቀን እንድናለን” አርሶ አደሮች
Next article“ሁልጊዜም ስለ ሰላም ልንሠራ ይገባል” የሀራ ከተማ የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች