“እኛም ፍላጎታችን እርቅ እንዲደረግ ነው፣ እርቅ ቢደረግ ከሰቀቀን እንድናለን” አርሶ አደሮች

11

ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንድ ዓመት ሊሞላው ሳምንታት የቀሩት ግጭት በአማራ ክልል ተፈጠሮ ከርሟል። በግጭቱ ሕይወት ጠፍቷል፤ ሀብት ወድሟል፤ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ተገድቧል።

ይህን ችግር ለመፍታት ሰላማዊ ውይይት እንዲኖር ጥሪ ሲቀርብ ቆይቷል። “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል ሐሳብ በአማራ ክልል ለተፈጠረው ችግር የመፍትሔ ሃሳብ ያመጣሉ ተብለው ከተመረጡ የማኅበረተሰብ ክፍሎች ጋር ተደጋጋሚ ምክክሮች እየተካሄዱ ነው።

ክልላዊ የሰላም ኮንፈረስ ከተካሄደ በኋላ ያለ ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ደረጃ፣ በየትኛውም ቦታ፣ በየትኛውም አደራደሪ ዘላቂ ተኩስ ለማቆም ንግግር እንዲደረግ የሚል ውሳኔ መደረሱ ይታወሳል። በክልላዊ ጉባዔው ውሳኔ መሠረት 15 አባላት ያሉት አመቻች የሰላም ካውንስልም ተመርጧል።

የሰላም ካውንስሉም ወደ ሥራ ገብቷል። የሰላም ካውንስሉ ባወጣው መግለጫ የአማራ ክልል ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድሞቹ ጋር በመኾን ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከተው ሚና ከፍተኛ መኾኑን ማንሳቱ ይታወሳል። ካውንስሉ በርካታ ኃላፊነት እና ተግባራት እንዳሉበትም ገልጿል።

የተቋቋመበትን ዓላማ እና ሥልጣን ሲገልጽም ካውንስሉ በሁለቱም ወገኖች እስካልተመረጠ ድረስ አመቻች እንጂ አደራዳሪ አይደለም። አመቻች ማለት ሁለቱ ወገኖች እኩል ድርድር እና ንግግር እንዲቀበሉ አደራዳሪ እና ተደራዳሪ እንዲመርጡ ቦታ እና ጊዜ እንዲወስኑ ፤ እየተጎዳ ያለው ማኅበረሰብ ከፍል ግምት ውስጥ አስገብተው ተኩስ አቁመው እንዲነጋገሩ የማግባባት እና የማመቻቸው ሥራ ይሠራል ማለት ነው። ካውንስሉ ለየትኛውም ወገን ማዳላት ሳያሳይ በየትኛውም ወገን ጫና ሳይደረግበት ሁለቱም ወገኖች በቅንነት እንዲቀራረቡ እና እንዲደራደሩ የአመቻችነት ሚናውን ይወጣል፤ ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነት አያስተናግድም፤ በጉባኤው ማደማደሚያ መሰረት ሥራውን ይወጣል ብሏል።

ሰላም የሁሉም ጉዳይ ነው፤ ሰላም የሁሉም ከሁሉም ነው ማለቱ ይታወሳል። የሰላም ካውንስሉ ያቀረበው የሰላም ጥሪ በአዎንታዊ መልኩ እንዲታይለት አደራ ብሏል። የሀገራችንን ሰላም በጋራ እናምጣ፣ የወንድማማቾች መገዳደል ይብቃ በማለት የሰላም ካውንስሉ ጥሪ ማቅረቡም ይታወሳል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ አርሶ አደሮችም ግጭት እንዲበቃ፣ ሰላም እንዲመጣ በሰላም አርሰው እና አፍሰው ሀገር እንዲመግቡ ጠይቀዋል። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ለሁሉም ነገር ቀዳሚ ሰላም መኾኑን ገልጸዋል። የጸጥታው ስጋት ፈተና ኾኖብናል ያሉት አርሶ አደሩ ወደ ገበያ ለመውጣት፣ ግብዓት ለማውጣት እንሰጋለን ነው ያሉት።

የጸጥታው ችግር ለአርሶ አደሮች ፈተና መኾኑን ነው ያነሱት። ወጥቶ ለመግባት ሰቀቀን መኾኑንም ገልጸዋል። በየመንገዱ ምን እንደሚደርስብን አናውቅም፤ ይህ ደግሞ እየፈተንን ነው ብለዋል። ፍላጎታችን እርቅ እንዲደረግ ነው፤ እርቅ ቢደረግ ከሰቀቀን እንድናለን ብለዋል።

ሕዝቡ በሰላም ችግር በፈተና ውስጥ እየኖረ መኾኑንም ገልጸዋል። በግብዓት በኩል እንዳመሰገነው ሁሉ ሰላሙም ተስተካክሎ የምናመሰግንበት ጊዜ እንዲመጣ እንፈልጋለንም ብለዋል። በአካባቢያቸው ከታጠቁ ኃይሎች ግብር እንደተጣሉባቸውም ገልጸዋል። ሕዝቡ መላ አጥቶ እየተቸገረ መኾኑንም አንስተዋል። እርቅ መደረግ አለበት፤ አምላክ ተጨምሮበት እርቅ እንዲወርድ ምኞታችን ነው፣ ሰላም ቢያድርልን ደስታችን ወስን አልነበረም ብለዋል።

ነዋሪነታቸው በሰሜን ሸዋ ዞን የኾነ አርሶ አደርም የሰላም ጉዳይ አሳሳቢ ኾኗል ብለዋል። ነጻ ኾነን ለመሥራት እና በሰላም ወጥተን ለመግባት ተቸግረናል ነው ያሉት። ሰላም ከሌለ ምንም ነገር እንደሌለም አንስተዋል። ሰላም አግኝተን ሥራችን እንድንሥራ እንፈልጋለንም ብለዋል። ለማልማት እና ለመኖር ሰላም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

አርሶ አደር ሰላምን ይፈልጋል፤ አንደኛው ከሌላኛው የሚያጋድል ሀሳብ መቆም አለበት። መገዳደል ይበቃል፤ ሰላም ነው የሚያስፈልግ ብለዋል። ወንድም ከወንደሙ እንዲታረቅ፣ ደም መፍሰስ እንዲቆም፣ እኛም ያለ ስጋት እንድንሠራ እርቅ እና ሰላም እንሻለን ነው ያሉት።

ያለ ሰላም የሚፈጸም ነገር የለም፤ ሁሉም ለሰላም እጁን ቢዘረጋ፣ ለሰላም መገንቢያ ጠጠር ቢጥል መልካም ነው ብለዋል አርሶ አደሪ። ማንኛውም አካል ቅድሚያ ለሰላም መስጠት አለበት፤ ለእኛ ሀገር ማንም አይመጣልንም፤ እኛው ተስማምተን ሁሉም የድርሻውን ወስዶ ለሰላም መሥራት አለበት ነው ያሉት።
አባቶቻችን ሀገር ያቆዩልን እርስ በእርስ እየተገዳደሉ አይደለም፤ አንደኛው ሲያጠፋ አንተም ተው አንተም ተው እየተባባሉ እያስታረቁ፣ ደም እያደረቁ ነው ይላሉ። የእስካሁኑ መገዳደል ይበቃል፣ አርሰን ለምንበላው እና ለምንበላው አርሶ አደሮች ስላም ሊሰጡን ይገባል ብለዋል።

አርሶ አደር ጸብ እና የሰላም መናወጥ አይፈልግም፣ ለአርሶ አደር የሚያስብ እና የሚቆረቆር ካለ ለሰላም እጁን መዘርጋት፣ ሰላምን ማስቀደም አለበት ብለዋል። ሰላም ይሁን ብሎ የሚሠራን ሁሉ መደገፍ አንጂ መንቀፍ የተገባ አይደለም፣ ሰላም ከሰቀቀን እና ከችግር ያድናል እንጂ አይጎዳም ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰቆጣ ከተማ በ134 ሚሊየን ብር ወጭ የተገነቡ ፕሮጀክቶችን ተመረቁ።
Next articleበበጀት ዓመቱ 14 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።