
ሰቆጣ: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሰቆጣ ከተማ ውስጥ የተገነቡ ድልድዮች፣ የድጋፍ ግንባታዎች እና የሥራ እድል መፍጠሪያ ሸዶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
ወይዘሮ ዘነቡ ጌታሁን የሰቆጣ ከተማ ፈንዲቃ ነዋሪ ሲኾኑ ድልድይ ባለመኖሩ ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጡ እንደነበር ገልጸዋል። ድልድዩ በመገንባቱ በተለይም የአቅመ ደካሞችን እና የህጻናትን ችግር የቀረፈ ነው ብለዋል። በክረምት ወቅት ጎርፍ ያስቸግራቸው እንደነበር የተናገሩት ደግሞ አቶ የኋላው ሞላ ናቸው። በፈንዲቃ ቀበሌ የመብራት፣ የውኃ እና የድልድይ መሰረተ ልማት በመሟላቱ መደሰታቸውንም ገልጸዋል። ለዘመናት የጠየቅነውን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ተፈትቶልናል ሲሉም ተናግረዋል።
የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መላሽ ወርቃለም ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች 134 ሚሊየን ብር ወጭ መደረጉን ገልጸዋል። ሁለት ድልድዮች፣ የድጋፍ ግንባታዎች፣ ሸዶች እና 16 ኮንቲነሮችን በአጠቃላይ 17 ፕሮጀክቶችን ማስመረቃቸውን ገልጸዋል።
ድልድዮቹ ለሰቆጣ ከተማ ሕዝብ ወሳኝ አገልግሎት ይሰጣሉ ነው ያሉት ከንቲባው። ሸዶች ደግሞ ሥራ አጥ ወጣቶች ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላሉ ብለዋል። በቀጣይም የወለህ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ቀሪ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት መንግሥት የኅብረተሰቡን የመልማት ጥያቄ ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከኅብረተሰቡ የተሠበሠበው ግብር መሰል ልማቶችን በከተማ አሥተዳደሩ አቅም ለመገንባት ያግዛል ብለዋል። በቀጣይም መሰል ልማቶችን መሥራታችንን እንቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡም የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅ እና በመንከባከብ ለጋራ ተጠቃሚነት የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!