
ደብረ ማርቆስ: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጤና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሰኔ 25/2016 ዓ.ም ጀምሮ በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ክትባት ላልወሰዱ ሕጻናት ክትባት ለመስጠት ዘመቻ መጀመሩ ነው የተገለጸው።
በምሥራቅ ጎጃም ዞንም በተለያዩ ምክንያቶች ክትባት ላልጀመሩ እና ክትባቱን ጀምረው ላቋረጡ ሕጻናት በዘመቻ ክትባት እየሰጠ መኾኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ የሺዋስ አንዱዓለም ተናግረዋል።
በዞኑ ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ከ292ሺህ በላይ ሕጻናትን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ የዘመቻ ሥራ መጀመሩን የገለጹት ኀላፊው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ180ሺህ በላይ ሕጻናት ክትባቱን መውሰዳቸውን ተናግረዋል። ክትባቱ ቤት ለቤት እና በጤና ተቋማት እየተሰጠ ይገኛል።
በዞኑ ምንም አይነት ክትባት ያልጀመሩ ከ20ሺህ በላይ ሕጻናት በልየታ መገኘታቸውም ተገልጿል።
እንደ አቶ የሺዋስ ገለጻ የተፈጠረው የሰላም እጦት በጤና አገልግሎቱ ላይ ችግር ፈጥሮ ቢቆይም አሁን ላይ በተገኘው አንፃራዊ ሰላም ችግሮችን ተቋቁሞ በዞኑ የሚገኙ ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናት ክትባት እንዲያገኙ እየተሠራ ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡ ሕጻናትን ወደ ጤና ተቋማት በመውሰድ ክትባት እንዲወስዱ ማድረግ እንደሚገባውም አሳስበዋል።
የክትባት ዘመቻውን ውጤታማ ለማድረግ ከጤና ባለሙያዎች፣ ወላጆች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም መምሪያው አስታውቋል።
ዘጋቢ፦ ግብረወርቅ ጌታቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!