
ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥነ ሕዝብ ድርጅት ኢትዮጵያ ያለ እድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል ለሠራችው ውጤታማ ሥራ ዕውቅና ሰጥቷታል።
የሴቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) በትናንትናው እለት ከአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ ከሚገኘው የመንግሥታት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት ተገኝተው ሽልማቱን ተቀብለዋል፡፡ ሚኒስትሯ የኢትዮጵያ መንግሥት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ የወሰዳቸውን የሕግ፣ የፖሊሲ እና የፕሮግራም እርምጃዎች አብራርተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በማኀበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ ዕውቅና እና ሽልማቱ መንግሥት ለሥርዓተ ፆታ እኩልነት እና ሴቶችን ለማብቃት ያለውን ቁርጠኝነት የበለጠ የሚያጠናክር እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ፣ የተባበሩት መንግሥታት ሥነ ሕዝብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ናታኒያ ካኔም እና ሌሎች የመንግሥታቱ ድርጅት አባል ሀገራት እና የዓለም አቀፍ ድርጅት የሥራ ኅላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ያለ እድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ የተቋቋመው ጥምረት እ.ኤ.አ በ2012 የተመሰረተ ሲኾን በጥምረቱ ውስጥ የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኀበራት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች፣ የምርምር ተቋማት እና የሃይማኖት ተቋማት ይገኛሉ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!