
ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቻይናዋ ሻንግሃይ ሲካሄድ ከቆየው የዘንድሮው ዓለማቀፍ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዐውደ ርዕይ ጎን ለጎን “ገቨርኒንግ ኤአይ ፎር ጉድ ኤንድ ፎር ኦል” በሚል መሪ መልዕክት ዓለማቀፍ የዘርፉ ምሁራን እና የቴክኖሎጂው መሪዎች የተገኙበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ማኅበራዊ ለውጥ በማምጣት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡ ነገር ግን እንደ ዲፕ ፌክ፣ በግላዊነት መብት እና በአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ዙሪያ ስጋቶችን ይዞ መምጣቱም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
እነዚህን መሰል ስጋቶች ለመቅረፍ ሀገራት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በውይይት እና በትብብር በመሥራት ከቴክኖሎጂው ጋር በተገናኘ ለሚመጡ አሥተዳደራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ መሻት እንደሚገባቸውም ተመላክቷል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዋና ጸሐፊው የቴክኖሎጂ ጉዳዮች መልዕክተኛ አማንዲፕ ሲንግ ጊል በመድረኩ ላይ ተገኝተው ዘርፉን በማሥተዳደር ረገድ የሚገጥሙ መሰናክሎችን የትኛውም ሀገር ብቻውን ሊጋፈጥ እንደማይገባ አስገንዝበዋል፡፡
ከቴክኖሎጂው ሁለንተናዊ ተጠቃሚ ለመኾን እና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዓለማቀፍ ትብብር አስፈላጊ ስለመኾኑ ማሳሰባቸውን ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!