ኢትዮጵያ የብሪክስ የልማት ባንክ አባል ለመኾን የምታደርገውን ጥረት ሩሲያ እንደምትደግፍ ገለጸች።

17

ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሩሲያ በብሪክስ የትብብር ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ አጠናክራ ለመቀጠል እንደምትሠራ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን ተናገሩ።

አምባሳደር ኤቭጌኒ ኢትዮጵያ ብሪክስን ከተቀላቀለች ጀምሮ በሚደረጉ ሁነቶች እያደረገች ያለው የነቃ ተሳትፎ የሚደነቅ ነው። ሩሲያ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት የብሪክስ ሊቀመንበር መሆኗን አስታውሰው፤ ጥምረቱን ማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ሁነቶችን እያካሄደች መኾኗን ጠቁመዋል።

ለአብነትም በቅርቡ የብሪክስ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የሌሎች ተቋማት ተወካዮች በሩሲያ ሞስኮ ከተማ ሥብሠባ መካሄዱን ገልጸዋል። በዚህም ሥብሠባ ኢትዮጵያ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጓን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በሙያተኞች እና ሚኒስትሮች ደረጃ የምታደርገው ተሳትፎ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ እንዲሁም ብሪክስን የሚያጠናክር መኾኑን ነው ያስረዱት።

ኢትዮጵያ በብሪክስ እያደረገች ያለው ተሳትፎ በትብብር ማዕቀፉ ለጋራ እድገት መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ መኾኑን አብራርተዋል። እንደ አምባሳደሩ ገለጻ አባል ሀገራቱ በሚቀይሱት የትብብር አቅጣጫ መሠረት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ የትብብር መስኮች አጋርነቷን ታጠናክራለች። ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የብሪክስ የልማት ባንክ አባል ለመኾን የምታደርገውን ጥረት ሩሲያ እንደምትደግፍም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2006 ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና “ብሪክ” የፈጠሩ ሲኾን በ2010 ደቡብ አፍሪካ ቡድኑን በመቀላቀሏ “ብሪክስ” ወደሚለው ስያሜ መጥቷል። ከዘንድሮ የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ይህንን በመስፋፋት ላይ ያለውን ጥምረት በይፋ ተቀላቅለዋል።

የብሪክስ አባል ሀገራት አሁን ላይ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሚኾነውን የዓለም ሕዝብ የሚይዙ ሲኾን፤ ይህም ከአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ ቁጥር አንጻር 45 በመቶ ማለት ነው። የሀገራቱ ምጣኔ ሃብት 28 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር ይገመታል። ይህም ከወቅታዊው የዓለም ምጣኔ ሃብት አንጻር ሲታይ 28 በመቶ መኾኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሰላም ካውንስሉ የሰላም ሀሳብ የዘገየ ቢኾንም ተገቢ እና አስፈላጊ ነው” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች
Next articleየሰው ሠራሽ አስተውሎት ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ከቴክኖሎጂው ጋር በተገናኘ ለሚመጡ ችግሮች የጋራ መፍትሔ መሻት እንደሚገባ ተገለጸ።