
ጎንደር: ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የመንግሥት ሠራተኞች ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከሚገኙ ክፍለ ከተሞች እና የቀበሌ አሥተዳደሮች የተውጣጡ የመንግሥት ሠራተኞች ተገኝተዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ ብሎም በጎንደር እና አካባቢው በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት የሰዎች ዕለታዊ የእንቅስቃሴ ሂደት ተጽዕኖ ውስጥ መውደቁን አስታውቀዋል።
የተፈጠረው የሰላም እጦት በሰብዓዊ እና በቁሳዊ ሃብቶች ላይ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ ያነሱት ተሳታፊዎቹ የመንግሥት ሠራተኞችም የጉዳቱ ሰለባዎች መኾናቸውን አንስተዋል። የሰላም እጦቱ ሁሉንም የሚጎዳ በመኾኑ ለመፍትሄው ሁሉም ሊሥራ ይገባል ብለዋል። ሁሉም የችግሩ ገፈት ቀማሽ መኾኑን በመገንዘብ የሰላም ካውንስሉ ያቀረበው ጥሪ ውጤታማ እንዲኾን ምሁራን እና በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ነው ያነሱት።
“እርስ በራሳችን እየተጠፋፋን በዚህ መንገድ ለውጥ ማምጣት አንችልም” ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች የቀረበውን የሰላም ጥሪ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ሁሉም አካላት ሊቀበሉት እንደሚገባቸው ነው ያስረዱት፡፡ የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች እንዳሉ የጠቀሱት ተወያዮቹ መንግሥት ጥያቄዎችን በመመለስ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባው ተናግረዋል።
በተጨማሪም አሁን ላይ በከተማው የተንሰራፋውን ሕገ ወጥ ተግባርን ለመከላከል ከጸጥታ አካላት ጋር ሕዝቡ ተባባሪ በመኾን ሊሠራ እንደሚገባው የመንግሥት ሠራተኞቹ መክረዋል። በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የጎንደር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቻላቸው ዳኘው ሰላምን ለማምጣት በመንግሥት በኩል ቁርጠኛ ኾኖ ለመሥራት ዝግጁ መኾኑን አስታውቀዋል።
በከተማው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተንሰራፋውን ሕገ ወጥ ተግባርን ለመከላከልም ከጸጥታ አካላት ጋር ሕዝቡ ተባባሪ በመኾን ሊሠራ እንደሚገባ ነው መልዕክት ያስተላለፉት።
ዘጋቢ:- ዳንኤል ወርቄ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!