
ባሕር ዳር: ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን የመንግሥት ሰራተኞች “ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልእክት በደባርቅ ከተማ ውይይት አካሂደዋል።
የውይይት መነሻ ያቀረቡት የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይመር ስዩም ባለፉት ዓመታት በነበረው የሰሜኑ ጦርነት እና በዞኑ ተከስቶ በነበረው ድርቅ ምክንያት ዞኑ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መኾኑን አስታውሰዋል። ከዚህ ችግር ሳናገግም ባለፈው አንድ ዓመት በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲፈጠር እና በማኅበረሰብ መካከል መጠራጠር እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።
በመኾኑም ክልሉ ካለበት የሠላም እጦት እንዲወጣ የመንግሥት ሰራተኛው የመፍትሔ ሃሳቦችን በማስቀመጥ ኀላፊነቱን መዋጣት አለበት ብለዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሰላም እጦት ዘር፣ሃይማኖት፣ ቀለም እና ሌሎች ልዩነቶችን ሳይለይ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚጎዳ በመኾኑ ስለሰላም መወያየት አስፈላጊ መኾኑን አንስተዋል።
የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ሳይፈቱ ለረጅም ዓመታት መቆየታቸው ለተፈጠረው ችግር መንስኤ ሊኾን እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈም የማንነት እና ወሰን ጉዳይ በጥንቃቄ መመራት እንደሚገባው አንስተዋል። የሰሜን ጎንደር ዞን ብልጽግና ፖርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ደማሙ ሀብቴ እንደተናገሩት ግጭት ሴቶችን፣ ሕጻናትን፣ አዛውንቶችን እና አካል ጉዳተኞችን በከፍተኛ መጠን የሚጎዳ በመኾኑ ለሰላም መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የድርድር እና የሰላም ጥሪውን ሁሉም ሲፈልገው የነበረ በመኾኑ ጫካ የገቡ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል አቶ ደማሙ ሀብቴ። ከማንነት እና ከወሰን ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። በአካባቢው የሚገኙ የሕወኃት ታጣቂዎች ከአካባቢው እንዲወጡ የማድረግ ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል።
የማንነት እና የወሰን ጥያቄውን ውጤታማ ለማድረግ የማኅበረሰቡ እና የመንግሥት ሰራተኛው ከአሉባልታ በመራቅ ከአመራሩ ጎን ኾኖ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል። የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሣ ዞኑ የተሻለ የሰላም አየር የነበረበት በመኾኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎች መከናወን ችለዋል ብለዋል።
አሁን ላይ እየተፈጠረ ያለው ችግር የነበረውን ሰላም የሚያጠፋ እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን የሚያደናቅፍ በመኾኑ ማንኛውም ማኅበረሰብ ለሰላም መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል። የተቋቋመውን የሰላም ካውንስል የምክክር ሃሳብ በመቀበል ጫካ የወጡ ወንድሞች ወደ ድርድር እንዲገቡ ለማድረግ ማኅበረሰቡ የድርሻውን ሊወጣ ይገባልም ነው ያሉት። በክልሉ የተፈጠረው ግጭት እንዲቆም እና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ውይይቶች እንደሚቀጥሉም ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!