“ሐምሌ 5 ለወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ነጻነት ዋጋ የከፈሉ ሰማዕታትን ለመዘከር የመታሰቢያ ሃውልት ለመገንባት መሠረተ ድንጋይ አስቀምጠናል” ከንቲባ አብደልውሀብ ማሞ

55

ሁመራ: ሐምሌ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ዝክረ ሐምሌ 5 ስምንተኛ ዓመት የመታሰቢያ መርሐ ግብር ታስቦ ውሏል።

ከከተማ አሥተዳደሩ የተወጣጡ የኅብረተሰብ ተወካዮች ከለውጥ በኃላ የተሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። ከጉብኝቱ በኃላ ለወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ነጻነት መስዋዕትነት ለከፈሉ ሰማዕታት የመታሰቢያ ሐውልት ለመገንባት የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጧል። በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ለሦስት አስርት ዓመታት አማራ ነኝ በማለቱ ከቀየው እንዲፈናቀል፣ ባሕል እና ወጉን እንዳያስቀጥል፣ በቋንቋው እንዳይናገር መከራ እና ግፍ ሲፈጸምበት መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሐምሌ 5 የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ የልደት ቀን ነው ያሉት የከተማዋ ነዋሪዎች ከነጻነት ማግስት ባሕል እና እሴታቸውን እያስቀጠሉ እንዲሁም በመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እየኾኑ መምጣታቸውን አንስተዋል። ያገኙትን ነጻነት አስጠብቀው ለመዝለቅ ከዞኑ መሪዎች ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አብደልውሀብ ማሞ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ከጭቆና አገዛዝ ነጻ ለመውጣት ከፋኝ ብሎ ሲታገል መቆየቱን አስታውሰዋል። ሐምሌ 5 /2008 ዓ.ም የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ የነጻነት ችቦ የተለኮሰበት መኾኑን አንስተው ለነጻነት ዋጋ የከፈሉ ሰማዕታትን ለመዘከር የመታሰቢያ ሃውልት ለመገንባት መሠረተ ድንጋይ መቀመጡን ገልጸዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ በሕዝብ ተሳትፎ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ፣ የጠጠር መንገድ ፣ የውኃ መፋሰሻ እና ሌሎች ግንባታዎችን ማከናወን እንደተቻለ ተናግረዋል። የከተማው ሕዝብ ከነጻነት ማግስት በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተጠቃሚ መኾኑን ገልጸው ሕዝቡ ነጻነቱን አስጠብቆ ለመዝለቅ የአካባቢውን ሰላም በንቃት እየጠበቀ ይገኛል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” በሚል ለወልቃይት ነጻነት ሲል በግፍ ለተሰዋው ወጣት አበበ ገረመው በስሙ ትምህርት ቤት ሊገነባ ነው፡፡
Next articleየጸጥታ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሰሜን ጎጃም ዞን መምህራን ተናገሩ።