“ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” በሚል ለወልቃይት ነጻነት ሲል በግፍ ለተሰዋው ወጣት አበበ ገረመው በስሙ ትምህርት ቤት ሊገነባ ነው፡፡

54

ባሕር ዳር: ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” በሚል ለወልቃይት ነጻነት ድምጹን ለማሰማት አደባባይ በወጣበት ጊዜ ነሐሴ 1/2008 ዓ.ም በግፍ የተገደለው ወጣት አበበ ገረመውን ለማሰብ ዛሬ በቃብትያ ሁመራ ወረዳ በስሙ ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጧል።

በመድረኩም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው፣ የዞኑ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረእግዚአብሔር ደሴ፣ የዞኑ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዋኘው ደሳለኝ፣ ከፍተኛ የዞኑ መሪዎች እና ነዋሪዎቹ ተገኝተዋል። የዞኑ አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የአማራነት ታሪክ መነሻ የኾነው እና በግፈኞች አያሌ መስዋዕትነት የከፈለው ወልቃይት እውነትን የያዘ አንድ ማንነት፣ እልፍ ጀግንነት፣ የማይናወጥ አማራነት፣ ሕይዎትን እስከ መስጠት የሚዘልቅ ማንነት ያለው ሕዝብ ነው ብለዋል።

ለነፃነት መላው የአማራ ሕዝብ እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ለዚህም ማሳያው “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ብሎ በባሕር ዳር ከተማ ለወገኖቹ ነፃነት ሲል በአደባባይ ሕይዎቱን የገበረው የነፃነት ታጋይ አበበ ገረመው አንዱ የነፃነት ችቦን የለኮስ ወጣት መኾኑን ገልጸዋል።

“የነፃነት ታጋዮች ዛሬ ላይ ሁነው ድሉን ባያዩትም እኛ እነሱን ስናስባቸው እና ስንዘክራቸው እንኖራለን” ብለዋል፡፡ ዛሬም የነፃነት ታጋይ ወጣት አበበ ገረመው መታሰቢያ የሚኾን ትምህርት ቤት በቃብትያ ሁመራ ወረዳ በስሙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሚገነባ ተናግረዋል። ትምህርት ቤቱም የአካባቢው ተወላጅ በኾነችው እና በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ አስተዋጽኦ እያደረገች ባለችው ወይዘሮ ዓለም አምባቸው ሙሉ ወጭ የሚገነባ መኾኑን አንስተው በአካባቢው ያለውን የትምህርት ቤት አጥረት እንደሚቀርፍም አስረድተዋል።

ትምህርት ቤቱ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ጠቁመው በቀጣይ ዓመት ግንቦት ወር እንደሚጠናቀቅም ጠቁመዋል። የሕወሓት የመጨረሻው ጥፋት በማይካድራ የፈፀመው የዘር ማጥፋት ቢኾንም የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለዓመታት ብዙ ማይካድራዎችን እያየ እና እየተፈጸመበት ለሦስት አሥርት ዓመታት ማሳለፉን አንስተዋል።

የእውነት ጊዜዋ ደረሰ እና በወልቃይት ምድር ግፍ እና መከራ፣ በደል እና ሰቆቃ ያበቃው በብዙዎች የሕይዎት መሰዋዕትነት እንደኾነ ገልጸው አሁንም ይህንን ነፃነት በሕግ አግባብ ለማረጋገጥ የሰማዕታት አደራን መጠበቅ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። ዛሬ በወልቃይቶች ምድር የመከራው ዘመን አብቅቷል፣ የመከፋቱ ጊዜ ቀርቷል ያሉት የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ነዋሪዎች ለዚህም የነፃነት ድል መላው የአማራ ሕዝብ ትግል መኾኑን አስረድተዋል።

የባሕር ዳሩ የነፃነት ታጋይ ወጣት አበበ ግርማው ወገኑ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ይደርስበት የነበረው ግፍ እና በደል አሳስቦት “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ብሎ በአደባባይ በወጣበት ጊዜ በግፈኞች ሕይዎቱ እንዲያልፍ መደረጉን አንስተዋል። በወጣቱ ሰማዕት ተሰይሞ የሚገነባው ትምህርት ቤት ለአካባቢው ተወላጆች የትምህርት ቤት እጥረትን በመፍታት እና የተማረ የሰው ኀይል በመገንባት የተሻለ ትውልድን ይፈጥራል ብለዋል።

እንደ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መረጃ ውድ የኾነ ሕይዎታቸውን ሰውተው የነፃነት ቀንዲል ባለቤት ያደረጉ የነፃነት ታጋይ ሰማዕታትን ቃል ማክበር ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡ ሰማቸውንም በተለያዩ የልማት ሥራዎች በማኖር ሁሌም እንዲታወሱ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የደቡብ ወሎ ዞን የመንግሥት ስራተኞች ተናገሩ።
Next article“ሐምሌ 5 ለወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ነጻነት ዋጋ የከፈሉ ሰማዕታትን ለመዘከር የመታሰቢያ ሃውልት ለመገንባት መሠረተ ድንጋይ አስቀምጠናል” ከንቲባ አብደልውሀብ ማሞ