
መተማ: ሐምሌ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ከዞኑ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ቢክስ ወርቄ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በነዋሪዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫና ማሳደሩን አንስተዋል። ችግሮች ከግጭት በራቀ አግባብ በውይይት እና በንግግር እንዲፈቱ መንግሥት ዝግጁ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ለተግባራዊ ተፈጻሚነቱ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የታጠቁ ኀይሎች የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ወደ ሰላም እንዲመለሱ የመንግሥት ሠራተኛው በኀላፊነት መሥራት እንዳለበትም ዋና አሥተዳዳሪው አሳስበዋል። እንደ ዋና አሥተዳዳሪው ገለጻ ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ሲባል ችግሮች በውይይት እና በንግግር እንዲፈቱ የመንግሥት ሠራተኛው ድርሻውን መወጣት አለበት ነው ያሉት፡፡
በተለይም የግጭትን አስከፊነትን በማስረዳት እና የችግር መውጫ መንገዱን በማሳየት ረገድም ሚናውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ሳይማር ያስተማረን ማኅበረሰብ ከገባበት ስቃይ እና እንግልት ለመታደግ ለሰላም አበክሮ መሥራት ተቀዳሚ ተግባር መኾን እንዳለበት የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በውይይት እና በድርድር እንዲፈታም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!