“ከ1 ሺህ 300 በላይ ጫካ የገቡ ኀይሎች ወደ ሰላማዊ ሕይዎት ተመልሰዋል” የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር

14

ባሕር ዳር: ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የመንግሥት ሠራተኞች ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡

በሰላም ኮንፈረንሱ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ “የወንድማማቾች መጠፋፋት ይብቃ፣ በሰላም ጎዳና የሚጓዝ እሱ ጀግና ሕዝብ ነው” ብለዋል፡፡ ግጭቱ የሕግ የበላይነት ትርጉምን በውል ባለመረዳት የሚሠሩ የልማት ሥራዎች የተቋረጡበት መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ከፍተኛ ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ውድመትም በዞኑ ስለማስከተሉ ነው ያብራሩት፡፡

መንግሥት ችግሮችን በውይይት እና በንግግር ለመፍታት ዝግጁ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው የሰላም ኮንፈረንስም ችግሮችን በመደማመጥ፣ በመነጋገር እና በመወያየት ለመፍታት የሚስችል ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡ የደቡብ ጎንደር ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንበር ክፈተው ለውይይቱ የሚኾን የመነሻ ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡

በመወያያ ጹሑፋቸውም እንዳሉት በዞኑ ከ1 ሺህ 300 በላይ ጫካ የገቡ ኀይሎች ወደ ሰላማዊ ሕይዎት ተመልሰዋል፡፡ ተወያዮቹ ባነሱት ሃሳብ እንዳሉት ክልሉን አሁን ካለበት የሰላም ችግር እንዲወጣ በክልል ደረጃ የተዋቀረውን የሰላም ካውንስል መደገፍ እና በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ከእውነት የራቀ ሃሳብ ይዘው ወሬ የሚያናፍሱ ሚዲያዎችን መገደብ ያስፈልጋል ያሉት ተወያዮቹ የመንግሥት ሠራተኛው በየአካባቢው ለሰላም የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንዲሁም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡ ውጤት በሌለው የሰላም እጦት ውስጥ ስለመቆየታቸው ተወያዮቹ ተናግረዋል፡፡ አካባቢውን የሰላም እና የልማት ቀጣና በማድረግ የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በበቂ ሁኔታ በመፈጸም ለሕዝብ ማሳየት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በውይይቱ ላይ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት የጦር አዛዦች፣ የዞኑ መምሪያ ኀላፊዎች እና የመንግሥት ሠራተኞች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ከደቡብ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም ካውንስሉ ጥረት እውን እንዲኾን መንግሥት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የራያ ቆቦ ወረዳ ነዎሪዎች ተናገሩ።
Next articleጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች እና የምግብ ዓይነቶች መወገዳቸውን ጤና ቢሮ አስታወቀ።