
ባሕር ዳር: ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጥሪ ሲያቀርቡ ዜጎች በከፍተኛ ተነሳሽነት በሥራው መሳተፋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
ዋናው ዓላማችን አካባቢያችንን ሳቢ በማድረግ መፀዳጃ ቤት የመጠቀም ባህላችንን ከመሠረቱ ማዳበር ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጥሪ ስናቀርብ ዜጎቻችን በከፍተኛ ተነሳሽነት በሥራው ተሳትፈዋል” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው ዛሬ በዜጎቻችን በዋጋ የማይተመን የልብ መዋጮ እና እምነት የተገነቡትን ሥራዎች በቦታው በመገኘት ገምግመናል ብለዋል።
ከፍተኛ ጥራት ባላቸው ጠንካራ እና ዘመን ተሻጋሪ በኾኑ ቁሶች በመጠቀም ደረጃቸውን የጠበቁ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ለመገንባት ቁርጠኝነት ይዘናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የሥራው መጀመሪያ ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልእክት በእናንተ ያላሰለሰ ድጋፍ የጀመርናቸውን ሥራዎች እናስፋፋለን ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!