
ጎንደር: ሐምሌ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተጀምሯል። በመርሐ ግብሩ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይን ጨምሮ የከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የክፍለ ከተማ መሪዎች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በችግኝ ተከላው የተሳተፉ ነዋሪዎች ችግኞችን ከመትከል ባሻገር ተንከባክቦ በማጽደቅ ረገድ ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበራ አደባ እንዳሉት በዘንድሮዉ የክረምት አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም የደን ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩም ከ 42 ሺህ በላይ ችግኞች ይተከላሉ ነዉ ያሉት አቶ አበራ። ከከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ያገኘነዉ መረጃ እንደሚያመላክተው በከተማ አሥተዳደሩ በአንድ ጀምበር በ12 የተከላ ቦታዎች በ23 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ 198 ሺህ ችግኝ ይተከላል ተብሎ ይጠበቃል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ መትከል ብቻ ሳይኾን የችግኞችን የጽድቀት መጠን መጨመር ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል። ባለፈው ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ ከ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ያስታወሱት አቶ ባዩህ የጽድቀት መጠናቸውም 89 በመቶ እንደነበር አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!