ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሀገራዊ የገጠር መንገድ ትስስር ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ መኾኑ ተገለጸ።

35

አዲስ አበባ: ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ407 ሚሊዮን ዶላር ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሀገራዊ የገጠር መንገድ ትስስር ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ መኾኑ ተገለጸ።

በዓለም ባንክ ድጋፍ እና በመንግሥት ትብብር በ407 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሀገራዊ የገጠር መንገድ ትስስር ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ መኾኑን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ገጠርን በመንገድ መሠረተ ልማት በማስተሳሰር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል እና በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን የምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ዕድገት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚረዳ ነው ብለዋል።

በገጠር የሚኖረውን ሕዝብ ተደራሽነት እና የእንቅስቃሴ ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ እና ጥገና ሥራን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማካሄድ የሚያስችል የልማት ማዕቀፍ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በሁሉም ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር ወደ 126 ወረዳዎች ፕሮጀክቱን ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁንም አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም ተጀምረው ያልተጨረሱ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የውስጥ መንገድን ከዋናው መንገድ የሚያገናኙ መንገዶችን በማስቀደም ይሠራል ብለዋል። ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በ2030 የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት ለመኾን ለምታደርገው ጉዞ ውጤታማነት አጋዥ እንደኾነም አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እንደ ዲፕሎማት በሕዝብ መታመን እና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ መኾን ተገቢ ነው” አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ
Next article“ሀገርን መስሪያ፣ ትውልድን መቅረጫ፣ ባሕል እና ወግን ማስተዋወቂያ ቀመሩ ሚዲያ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ