
ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌድሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች እስከ ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም የሚቆይ የቅድመ ስምሪት ሥልጠና መሥጠት ጀምሯል።
በሥልጠናው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አምባሳደር መኾን ሀገራዊ ኀላፊነትን እና የሕዝብ አደራን በትጋት የመወጣት ትልቅ ኀላፊነት ነው ብለዋል። “እንደ ዲፕሎማት በሕዝብ መታመን እና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ መኾን ተገቢ ነው” ብለዋል ሚኒስትሩ ።
የዘንድሮው የአምሳደሮች ሹመት ከየትኛም ጊዜ የተለየ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ሹመቱ የተሠጠው ሙሉ ለሙሉ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት መኾኑን ተናግረዋል። ሹመቱ ዕውቀትን እና ትጋትን መሠረት ያደረገ እንደኾነም ገልጸዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የውጭ ጉዳይ ሥራ ከዕውቀት፣ ክህሎት እና አስተውሎት ጋር በጽኑ የተጋመደ ነው።
የአምባሳደሮች ሹመት እንደ ሀገራት ይለያያል ያሉት አምባሳደር ታዬ፣ ተሿሚ አምባሳደሮች ከዚህ ቀደም ባሳዩት ሥራ የተመረጡ መኾናቸውን ገልጸዋል። ተሿሚ አምባሳደሮች ከፍ ያለ ሀገርን እና ሕዝብን የማገልገል ስሜት ሊኖራቸው እንደሚገባም አሳስበዋል። ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር መትጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!