የአማራ ክልል ምክር ቤት የኦዲት ግኝትን ዳር የሚያደርስ ቋሚ ኮሚቴ ሊያቋቋም ነው።

26

ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የአስረጂዎች መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር ”የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ” በሚቋቋምበት ቅድመ ሁኔታ ላይ ውይይት አድርጓል።

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ከክልሉ ፍርድ ቤት፣ የፍትሕ ቢሮ እና የዋና ኦዲተር ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የምክር ቤቱን የክትትል እና ቁጥጥር ሥርዓት ለማጠናከር ”የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ” ማቋቋም ማስፈለጉ ተገልጿል። በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) በዴሞክራሲ ልምምድ ውስጥ የተጠያቂነት ሥርዓት ለማምጣት በሕግ አውጪው ክፍል የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ የሚሠራው አንዱ ኦዲተር መሥሪያ ቤት ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት እስካሁን ያለው የአሠራር ልማድ የኦዲት ሥራ እና ግኝቶችን በበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይሠራ ነበር። ይህም አሠራር ገለልተኛ ተቋም ከመገንባት አኳያ ውስንነቶች እንደፈጠረ ገልጸዋል። የዋና ኦዲተር ሪፖርትን በገለልተኝነት መርምሮ ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አኳያ ”የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ” የማቋቋምን አስፈላጊነትም አብራርተዋል።

በውይይቱ የኦዲት ግኝት ዓለም አቀፍ የአሠራር አማራጮች፣ በአማራ ክልል የኦዲት ግኝትን የማስመለስ ውስንነት፣ የቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊነት እና ስለ አደረጃጀቱ የመነሻ ሃሳብ ቀርቦ ተብራርቷል። ቋሚ ኮሚቴው በክትትል እና ቁጥጥር ሥርዓቱ ተጠያቂነትን ጭምር ማስተግበር የሚያስችል ሥልጣን እና ተግባር እንዲኖሩት እንዲሁም የኦዲት ግኝት ሪፖርቶችን እየተከታተለ እና እየተቆጣጠረ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ መደበኛ ሥራው እንደሚኾን በመወያያ ሃሳቡ ቀርቧል።

👉 የሚቋቋመው ቋሚ ኮሚቴ የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተግባራትን እንዳይጋራ፣
👉 የኦዲት ግኝት ላይ ብቻ ሳይወሰን የዋና ኦዲተር አገልግሎት ሽፋንን እና ተደራሽነትንም እንዲከታተል፣
👉 በኦዲት ግኝት ላይ የምክር ቤት ውሳኔም መፈጸሙን እንዲከታተል፣
👉 ከዚህ በፊት የነበሩ የኦዲት ግኝቶች እልባት አለማግኘታቸውን ታሳቢ በማድረግ የሚቋቋመው ኮሚቴ ግን የሚያስፈጽምበት የተለየ ነገር ይዞ እንዲቋቋም
👉 በማቋቋሚያ ሕጉ ኦዲት አድራጊ እና ተደራጊ የሚግባቡበትን ሥርዓት እንዲበጅለት
👉 የኦዲት ግኝትን ለማስመለስ ተቋማት የሚቀናጁበት አሠራር የቋሚ ኮሚቴው የአሠራር አካል እንዲኾን የሚሉት ደግሞ ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል ናቸው።

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመንግሥት ፋይናንስ እና በጀት አሥተዳደር ሥርዓት ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ እና የኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤት ሪፖርት ቅጂ ለቋሚ ኮሚቴውም ደርሶት እና መርምሮ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ የሚቋቋመው ቋሚ ኮሚቴ ሥራ እንደሚኾንም ነው ዶክተር ደሴ ያብራሩት።

የቋሚ ኮሚቴው መቋቋም በክልሉ በጀትን በአግባቡ በመጠቀም በኩል ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ ሚናው የጎላ እንደሚኾን በውይይቱ መግባባት ላይ ተደርሷል። ዶክተር ደሴ የተሰጡ አስተያየቶች በግብዓትነት በመጠቀም ረቂቅ ሕጉን ለማዳበር እንደሚያገለግሉ ገልጸዋል። ቋሚ ኮሚቴው በምክር ቤቱ ተቋቁሞ ሲሠራ የመንግሥት ተቋማት የሚመደብላቸውን በጀት ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ድጋፍ በማድረግ፣ በመከታተል እና በመቆጣጠር እንዲሁም አላግባብ የባከነ ሃብትን በማስመለስ እና ተጠያቂነትን በማስፈን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የአማራ ክልል ምክር ቤትን ሚና ከፍ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“276 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ግብር ለመሠብሠብ እየተሠራ ነው” የጎንደር ከተማ አሥተዳደር
Next article“የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ወቅት ሥራችን ያስቀመጥነውን ግብ በሚያሳካ መልካም አጀማመር ላይ ይገኛል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)